ዩኒቨርሲቲዎች የክልሉን ቱሪዝም ልማት በምርምር እንዲያግዙ የደቡብ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ጠየቀ

3806

አርባምንጭ ሚያዝያ 27/2010 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከነባር ቅርሶችና ባህላዊ ትውፍቶች የሚገኘውን የቱሪዝም ገቢ ለማሳደግ በምርምር እንዲያግዙ የደቡብ የክልል ባህልና ቱሪዝም ልማት ቢሮ ጠየቀ።

በአርባ ምንጭ ከተማ እየተከበረ ባለው 3ኛው የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ፌስትቫል በባህል ልማት ዙሪያ በቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች ላይ ምሁራን እየተወያዩ ነው።

ከጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢዎች መካከል የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ተመስገን ንጉሴ “በክልሉ በህብረተሰቡ ጥበቃ የቆዩ ነባር ቅርሶች ለቱሪዝም ገቢ መጨመር ያላቸው ፋይዳ የጎላ ቢሆንም በትኩረት ማነስ የሚፈለገውን ጥቅም አላስገኙም” ብለዋል።

ይሁን እንጂ በህብረተሰቡ ጥበቃና እንክብካቤ የቱሪስቶችን ቀልብ የሳቡ የኮንሶ መልካዓ-ምድርን የመሳሰሉ ቅርሶች የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

“በተለይ ጥንታዊ ትክል ድንጋዮች፣ መካነ መቃብሮች፣ ዋሻዎችና የእርከን ስራዎች የያዟቸው ነባር እውቀቶችና ልምዶች ጎልተው እንዲወጡ ለቅርሶች ልማትና እድገት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል፡፡

ሌላኛው ጥናት አቅራቢ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ሳላሂ ሰይድ በበኩላቸው የክልሉ ብሔረሰቦች ትውፊታዊ የባህል እሴቶች የቱሪዝም መስህብነታቸው ጨምሯል።

በተለይ የማህበረሰቡ የአመጋገብ፣ አለባበስ፣ አጋጌጥና የባህል ጭፈራዎች በቱሪዝም ልማቱ እድገት ከፍተኛ ድርሻ ማበርከታቸውንና ለብዙዎችም የስራ መስክ ሆነው መገኘታቸውን ገልጸዋል።

እሴቶቹን ከዚህም በላይ ማልማት የሚያስችል እምቅ አቅም ያለው ዘርፍ በመሆኑ ተጨማሪ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ደርዛ እንደገለጹት ህብረተሰቡ ለባህሉና ትውፊቱ መልማት የሚያሳየው ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ ዩኒቨርሲቲው ዘርፉን በምርምር ለመደገፍ የሰው ኃይል እያሰለጠነ ይገኛል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አክመል መሃመድ በበኩላቸው ባህልና የባህል ቅርሶች በአግባቡ ለምተው ለማህበራዊ ጥቅም እንዲውሉ ቢሮው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲ ምሁራንም በቅርሶችና ባህላዊ እሴቶች ላይ የጀመሩትን የምርምርና የሙያ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በአርባምንጭ ከትላንት በስቲያ በተከፈተውና ዛሬም በቀጠለው ፌስቲቫል የክልሉ ብሔረሰቦች የባህል ቁሳቁሶችንና ቅርሶችን ለእይታ ያቀረቡ ሲሆን በተሳታፊዎችም ተጎብኝተዋል።