በአዲስ አበባ በ11 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የንግድ ማዕከል ስራ ጀመረ

77
ነሐሴ 30/2011 የሜድሮክ ቴክኖሎጂ እህት ኩባንያ የሆነው አዲስ ሆም ዴፖ አዲስ አበባ ውስጥ በ11 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው ዘመናዊ የንግድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ። የንግድ ማእከሉ የቤት፣ የቢሮ፣ የግንባታ እቃዎችን፣ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ እቃዎችን ለገበያ ያቀርባል። አዲስ የተገነባው  አዲስ ሆም ዴፖ ቅርንጫፍ የንግድ ማእከል ለ15 ኢትዮጵያዊያን የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ዓመታዊ የሽያጭ መጠኑም 150 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ የሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ፕሬዘዳንት ዶክተር አረጋ ይርዳዉ  ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ አዲስ ሆም ዴፖ ኩባንያ የጀመራቸዉ አሰራሮች  የተሻሉና የአለም አቀፍ የንግድ ማህበረሰብ የሚጠይቀዉን መስፈርት ያሟሉ  መሆኑን መታዘባቸዉን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ማህበረሰብም ከሌሎች ዓለም  አገራት ጋር ለመወዳደር  ዘመናዊ  የሆነ አደረጃጀትና አሰራር ለመዘርጋት ራሱን ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባዉ ገልፀዋል። አዲስ ሆም ዴፖ  በ1995 ዓም 15 ሰራተኞችን በመያዝ ሲቋቋም ካፒታሉ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን 167 ሰራተኞችን በመያዝ ዓመታዊ የሽያጭ መጠኑን ወደ 317 ሚሊዮን ብር አሳድጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም