ለሦስት ወራት የሚቆይ የደም ልገሳና ንቅናቄ መርሀ ግብር ይካሄዳል

70
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 በኢትዮጵያ ለሦስት ወር የሚቆይ የደም ልገሳና ንቅናቄ መርሀ ግብር ሊካሄድ ነው። ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ዛሬ የሚከበረውን የዓለም የደም ለጋሾችን ቀን ምክንያት በማድረግ በሰጠው መግለጫ፤ ከሰኔ 7 ጀምሮ  ለሦስት ወር የሚዘልቅ ሰፊ የደም ልገሳና ንቅናቄ ለማድረግ እቅድ መያዙን አስታውቋል። በዚህም መሰረት ሰኔ 10 ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ጋር በመተባበር በበጎ ፈቃድ ጎዳና ላይ የሚያስተባብሩ ሰዎች ደም የሚለግሱበት መርሃግበር ተዘጋጅቷል። በብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት የለጋሾች አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ተመስገን አበጀ እንደተናገሩት፤ ሰኔ 17 በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አማካኝነት ሰፊ የሆነ የደም ልገሳና ንቅናቄ ይካሄዳል። ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች የሚሰበሰበው የደም መጠን በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ዶክተር ተመስገን ተናግረዋል። ይሁንና ደም በከፍተኛ መጠን የሚፈልጉ የጉዳት ዓይነቶች በመኖራቸው አሁንም የሚሰበሰበው የደም መጠን በቂ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲያደርግ ጠይቀዋል። "ለሌሎች እንድረስ ደም እንለግስ ህይወት እናካፍል " በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት የተከበረውን  የዓለም የደም ለጋሾች ቀን አስመልክተው  የብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት አምባሳደር አቶ ውብሸት ወርቃለማው በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሽ ግለሰቦችንና ተቋማትን አመሰግነዋል። "የኢትዮዽያ ህዝብ ለልግስና ቅርብ በመሆኑ በቂ ቅስቀሳ ከተደረገና ምቹ  አጋጣሚ ከተፈጠረ የተፈለገውን ያህል ደም ለመሰብሰብ አይከብድም" ሲሉ ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ጠንክሮ እንዲሰራ አሳስበዋል ። ለሦስት ወራት በሚቆየው የደም ልገሳና ንቅናቄ መርሀ ግብር  የእግር ጉዞ  መርሃግበር ፕሮግራም  እንዲሁም ደም በመለገስ የሚታደሙበት  የሙዚቃ ኮንሰርት እንደሚዘጋጅም ዶክተር ተመስገን ገልጸዋል። በበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ ላይ የተመሰረቱ ክበቦች የእግር ኳስ ጨዋታ ለማድረግ መርሃ ግብር መያዙንም ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ  ከአንድ መቶ በላይ ለበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች የእውቅናና የምስጋና መርሃግብር ይዘጋጃል። ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ከአስሩም ክፍለ ከተሞች ወጣቶች ጋር በመተባበር የአደባባይ የደም ማሰባሰብ ተግባር እንደሚያከናውንም ተጠቁሟል። ታዋቂ ሰዎች የሚሳተፉበት የክልል የግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ መድረኮች በተመረጡ የክልል ከተሞች ይዘጋጃሉም ተብሏል። የኢትዮዽያ የደም ባንክ አገልግሎት በ1962 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ስር ሆኖ አገልግሎቱን የጀመረ ሲሆን፤ ከ 2007 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ራሱን ችሎ በአዋጅ ተቋቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም