በአማራ ክልል ከደረሱት ጥቆማዎች መካከል 529ኙ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መሆናቸው ተረጋግጧል --- ኮሚሽኑ

70
ባህር ዳር ሰኔ 7/2010 በአማራ ክልል ከህብረተሰቡ ከደረሱት ጥቆማዎች መካከል 529ኙ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መሆናቸውን ማረጋገጡን የክልሉ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ። በተሰጣቸው የይቅርታ ጊዜ ተጠቅመው ራሳቸውን ያጋለጡ 532 ሰዎችም የስቪል ሰርቪስ መደቡ በሚፈቅድላቸው የስራ መደቦች እንዲመደቡ ተደርጓል። ኮሚሽነር ዝጋለ ገበየሁ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ህገ ወጥ የትምህርት ማስረጃዎችን ለማምከን ለአንድ ዓመት ያህል በተደራጀ መንገድ ሲሰራ ቆይቷል። በተደረገው የህገ ወጥ ትምህርት ማስረጃ ማስወገድ ዘመቻም ከ334 የመንግስትና የግል ትምህርት ተቋማት ተወስዷል የተባለ 5 ሺህ 55 የትምህርት ማስረጃ ጥቆማዎች ከህበረተሰቡ እንደደረሰው ተናግረዋል። የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግም ትክክለኛነቱን ለማጣራት ለትምህርት ተቋማት ከተላከው 4 ሺህ 595 ጥቆማዎች ውስጥ 2 ሺህ 779ኙ ምላሽ ማግኘቱን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። “ምላሽ ከተሰጠው ውስጥ 81 ከመቶ የሚሆነው የትምህርት ማስረጃ በተቋማት ተምረዋል የሚል ምላሽ አግኝተዋል'' ብለዋል። ቀሪው 19 ከመቶ ወይም 529ኙ የትምህርት ማስረጃ የተጭበረበረ መሆኑን ማረጋገጥ እንደተቻለ አብራርተዋል። ከነዚህ ውስጥም 63 መዝገቦች ምርመራቸው ተጠናቆ ለአቃቢ ህግ መላኩን ጠቁመው፤ ሌሎች የትምህርት ማስረጃዎችን የማጣራት ስራ በተጠናከረ መንገድ መቀጠሉን ገልፀዋል። በ91 የትምህርት ተቋማት በጥቆማ የተገኙ የ461 የትምህርት ማስረጃዎች ተቋማቱ ቋሚ አድራሻ ማግኘት ባለመቻሉ ማስረጃውን ለማረጋገጥ መቸገሩን ኮሚሽነሩ አመልክተዋል። እንዲሁም ከአልፋ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅና ከአገር አቀፍ የፈተናዎች ድርጅት ተሰጥተዋል የተባሉ አንድ ሺህ 284 የትምህርት ማስረጃዎች ተቋማቱ በወቅቱ መልስ መስጠት ባለመቻላቸው ማረጋጋጥ አንዳልቻሉም ኮሚሽነር ዝግአለ አስታውቀዋል። “የሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ተከታትሎ ለማምከን በተደረገው የዘመቻ ስራ የትምህርት ተቋማት ኃላፊነት ተሰምቷቸው ፈጣን ምላሽ ያለመስጠት፣ የቀናነት መጓደልና ትብብር ያለማድረግ የፀረ ሙስና ትግሉን ፈተና አድርጎታል'' ብለዋል። በመሆኑም የተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃንም ሆነ ሌሎች የሃገር እድገት ፀር የሆኑ የሙስና እንቅስቃሴዎችን በአንድ ተቋም አቅም ብቻ መከላከል የሚቻል ባለመሆኑ ሁሉም አካል ችግሩን ለመከላከል ሊሰራ እንደሚገባው አሳስበዋል። በተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ ሲገለገሉ የተገኙ ግለሰቦችም ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ጠቁመዋል። ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን የማምከን ተግባርም በተሰጣቸው የይቅርታ ጊዜ ተጠቅመው ራሳቸውን በፈቃዳቸው ያጋለጡ 532 ሰዎች ስቪል ሰርቪስ በሚፈቅድላቸው የስራ መደቦች እንዲመደቡ መደረጉን ጨምረው አስታውቀዋል። ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ለመከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ከሰኔ 15 እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም በይቅርታና በጥቆማ ጊዜ የተጀመረ መሆኑ ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም