በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ውጤታማ የሆነው ወጣት አርሶ አደር ተከታዮችን እያፈራ ነው

76
ጎባ ነሐሴ 30/2011፡ -በባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ የውሃ አማራጮችን ተጠቅሞ በጀመረው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ውጤታማ የሆነው ወጣት አርሶ አደር ተከታዮችን እያፈራ መሆኑን ገለጸ። ወጣቱ በወረዳው ዝናብ አጠር አካባቢዎች ከሚኖሩ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ሲሆን የሚኖረው በከተቲ ቀበሌ ውስጥ ነው። ታሲሳ ንጉሴ የተባለው ይሄው ወጣቱ አርሶ አደር በምሰራቅ ሸዋ ዞን መቂ አካባቢ በቀን ሰራተኝነት ተቀጥሮ ይሰራበት በነበረበት ወቅት በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ያገኘውን ልምድ በማምጣት በሶስት ሄክታር ማሳ ላይ የቲማቲም ፣ፓፓያና የሽንኩርት ምርት ማልማት ይጀምራል። ከአንድ ዓመት ወዲህ የጀመረው ይሄው ልማት የዝናብ ውሃን እያቆረ በሞተር ፓምፕ በመሰብና ሌሎች የውሃ አማራጮችን ተጠቅሞ ነው። ወጣቶ ለኢዜአ እንዳለው ከሚያለማው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በአንድ የምርት ወቅት ሽያጭ እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ስራውን ይቀጥላል። እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴም ያመረተው ቲማቲም በ22 የጭነት አይሱዙ ተሽከርካሪ ለገበያ በማቅረብ ከሽያጩ ከ1 ሚሊዮን 800ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል። በእቅድ የያዘውን ገቢ ከቲማቲም ምርት ሽያጭ ብቻ መሸፈን እንደሚችል ያመለከተው ወጣቱ የሽንኩርትና የፓፓያ ምርት በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ ስለሚገኙ የተሻለ ውጤት እንደሚጠብቅ ገልጿል። ውጤታማነቱን ያዩ ተከታዮች ከማፍራቱም ሌላ በልማት ከ30 ለሚበልጡ የአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ችሏል። በቀጣይ ልማቱን በማስፋት ሌሎች በአካባቢው ያልተዳሰሱ የልማት ስራዎች ላይ ለመሰማራት እቅድ እንዳለው ወጣቱ ተናግሯል። በቀበሌው በሴፍትኔት መርሃ ግብር ከታቀፉ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሱልጣን ከብር ሁሴን በበኩላቸው ከዚህ በፊት የዝናብ ውሃን ብቻ በመጠበቅ ከሚያመርቱት የዘንጋዳና የበቆሎ ምርቶች የቤተሰባቸውን የምግብ ፍጆታ ለማሟላት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሷል፡፡ በአካባቢው ተወጣት ታሲሳ ተሞክሮ ተከትለው  የዝናብ ውሃን በማቆር የጀመሩት  የአትክልትና  ፍራፍሬ ልማት ወደ ራሳቸው ማሳ በማስፋት በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ ቲማቲም ፣ ሙዝና ሽንኩርት በማልማት ከእርዳታ ጠባቂነት ለመውጣት መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። ቲማቲም ጨምሮ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ማካሃድ ልምድ ያገኙት ያገኘሁት ከታሲሳ ነው፤ አሁን በልማቱ በመሳተፍ በተሸለ ደረጃ ላይ ነው ያለሁት። ከቲማቲም በተጓዳኝ ሙዝ፣ ሽንኩርትና ሌሎችም እያለማሁ ነው፤ ሌሎች አርሶ አደሮችም የኔን ፈለግ እንድከተሉ እመክረለሁ። “ የዝናብ ውሃን በማቆር በሄክታር መሬት ላይ ሽንኩርት በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት በሚያገኙት  ገቢ መኖሪያ ቤታቸውን ከሳር ክዳን ወደ ቆርቆሮ ቤት መቀየራቸውና ልጆቻቸውንም በአግባቡ እያስተማሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው በልማቱ እየተሳተፉ ያሉ አርሶ አደር ሙክታር ጀማል ናቸው። አርሶ አደሩ እንዳሉት በቀጣይ በሞተር ፓምፕ በመታገዝ በአካባቢያቸው የሚገኙ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ልማቱን አስፋፍተው ከጠባቂነት ለመላቀቅ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በአካባቢያችን ከዚህ በፊት የሚገኙ የውሃ አማራጮችን የመጠቀም ልምዱ አነስተኛ ነበር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመስኖ ልማት በመሳተፍ በዓመት ሁለት ጊዜ እያመረትን እንገኘለን። በዚህም ከአንድ ጥማድ አስር ኩንታል ሽንኩርት በማምረት ተጠቃሚ እየሆን ነው። ኑሮችንንም እያሻሻልን  ነው። በጊኒር ወረዳ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብበት ልማት የመስኖ ኤክስቴንሽን ባለሙያ አቶ አብዱረህማን በከር እንዳሉት በወረዳው በሁለት ዙር የመስኖ ልማት ወቅት ከ4ሺህ ሄከታር የሚበልጥ መሬት በአትክልትና ፍራፍሬዎች እየለማ ይገኛል። የባሌ ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደውድ አብዱሪ በበኩላቸው በዞኑ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር የውሃ አማራጮች እምቅ አቅም ቢኖረውም አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ በመስኖ ልማት በማሳተፍ በኩል ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገበሬው በመደበኛነት ከሚያመርተው የሰብል ልማት በተጓዳኝ በአካባቢው የሚገኘውን የውሃ አማራጮችን ተጠቅሞ በመስኖ ልማት ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ ነው።   እስካሁን በተደረገ ጥረትም ከ78ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ እየለማ መሆኑን ያመለከተየት ኃላፊው ከዚህም ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም