የፈረንሳይ የእሳት አደጋ ባለሙያ ቡድን  በአማዞን ደን የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለማጥፋት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተሰማ

105
ነሀሴ /2011ፈረንሳይ በደቡብ አሜሪካ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመታደግ በስድስት የባለሙያዎች ቡድን የተዋቀሩ 40 የእሳት አደጋ ባለሙያዎችን በመላክ እገዛ እንደምታደርግ ተነገረ፡፡ በቦልቪያና ብራዚል ድንበር አካባቢ የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋት ፈረንሳይ በብቁና የተሟላ የሰው ሃይል የታገዙ አራት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እንደምትልክም ነው መረጃው ያመለከተው፡፡ እንዲሁም ቦልቪያ ባለፈው ሳምንት ለአውሮፓ ህብረት የሲቪል ጥበቃ መስሪያ ቤት  ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ድጋፍ እየተደረገላት ይገኛል ተብሏል፡፡ የባለሙያዎች ቡድኑም መነሻውን የቤልጂየሟ ዋና ከተማ ብራስልስን በማድረግ  ከፈረንሣይ፣ ከስፔን እና ከዴንማርክ የተውጣጡ ሰባት ባለሙያዎችን በማቀፍ ወደ ቦሊቪያ ጉዞ መጀመራቸውን መረጃው ጠቁሟል፡፡ ይህም የአውሮፓ ህብረት ከሌላው ዓለም ጋር ያለውን አንድነት የሚያሳይ እንደሆነ ዘገባው አስፍሯል፡፡ የተፈጥሮ አደጋ ድንበር የለሽ ሲሆን እየሰፋ ሲመጣ ደግሞ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖው መጠነ-ሰፊ መሆኑን  ዘገባው አክሏል፡፡ ድጋፍ ያሳዩ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ደግሞ በአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ ዕርዳታና ቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ከሪስቶስ ስታይሊኒደስ መሆናቸውን  በመራጃው ሰፍሯል፡፡ የሰብዓዊ ዕርዳታ እና ቀውስ አመራር ኮሚሽነር የሆኑት ክሪስቶስ ስታይሊኒደስ በማከልም የአውሮፓ ህብረት  ከቦሊቪያ እና በአማዞን ቀጠና ካሉ ሁሉም ሀገራት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረት የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ  ኮፐርኒከስ  ሳተላይት  አገልግሎት በማካሄድ በአሁኑ ጊዜ በደን የእሳት አደጋ የተመቱ ቦታዎችን ካርታ እየሰጠ እንደሚገኝም ዘገባው አስፍሯል፡፡(ዩሮ-ኒውስ)
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም