በአዳማ ከተማ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የልማት ሥራዎች ይከናወናሉ

63
አዳማ (ኢዜአ) ነህሴ 29 ቀን 2011በአዳማ ከተማ በበጀት ዓመቱ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 47 የመሰረተ ልማት   ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ እንደሚካናወን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ገለጹ። የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሙሀመድ ከማል ለኢዜአ እንደገለጹት ፕሮጀክቶቹ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ ናቸው። የአስፋልት፣ የጌጠኛ ድንጋይና የጠጠር መንገዶች እንዲሁም በአዳዲስ የከተማዋ ቀበሌዎች የኃይል አቅርቦት ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ በፕሮጀክቶቹ የተካተቱ ናችው። የትምህርትና የጤና ተቋማት ግንባታ፣ የጽዳትና ከተማዋን የማስዋብ ሥራዎችን ጨምሮ ለሚከናወኑ 47 የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡንም አቶ ሙሀመድ ገልጸዋል። በከተማዋ የመሰረተ ልማት አቅርቦት አለመሟላት የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱን የተናገሩት አቶ ሙሀመድ "ሀገራዊ ለውጡን ከዳር ማድረስ የሚቻለው የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲቻል ነው" ብለዋል። ከመሰረተልማት ሥራው በተጨማሪ ለ15 ሺህ የከተማዋ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎችን የመለየት ሥራ እንደሚሰራም አመልክተዋል። በግንባታ ላይ ያሉትን የማህበራት ሠርቶ ማሳያዎችን አጠናቆ ማስተላለፍና ለማህበራት የብድር አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ተደራሽ የማድረግ ሥራ በበጀት ዓመቱ በቁልፍ ተግባር እንደሚከናወኑም አመልክተዋል። ይህን እቅድ ለማሳካት ከአስተዳደሩ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉት ፈጻሚዎች ያሉባቸውን የአቅም፣ የአመለካከትና የክህሎት ክፍተት ለመሙላት እየተሰራ ነው ሲሉም ገልጸዋል። ከእዚህ በተጨማሪ ስለሚከናወኑ ሥራዎች ከወዲሁ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የስልጠናና አቅም ግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግርዋል። በከተማዋ ሰላምና ፀጥታን ማስፈን፣ የህግ የበላይነትን ማስከበር፣ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ማስወገድ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ  የበጀት ዓመቱ አብይ ሥራዎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት የአቅም ግንባታ ስልጠና ከአመራሮች ጀምሮ እስከ ፈጻሚ ድረስ እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአዳማ ከተማ የኦዴፓ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ቢራሳ ናቸው። በየደረጃው የተቀናጀና የተደራጀ የለውጥ ሠራዊት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ይህም በከተማዋ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በአስፈጻሚና ፈፃሚዎች ዘንድ የሚታየውን የአመለካከት፣ የአስተሳሰብና የአቅም ችግሮች ለማስውገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልልጸዋል። አቶ አዳና እንዳሉት የፍትህ ሴክተርና የማዘጋጀ ቤት አገልግሎት አሰጣጥን ፈጣንና ቀልጠፋ በማድረግ፣ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በጥራት በማከናወንና በተቀመጠው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በማድረግ የህብረተሰቡን እርካታ ማምጣት ቀዳሚ አጀንዳ ነው። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የመሪ ድርጅቱ ኦዴፓ የ2012 ዓ.ም ዕቅድ ላይ በየደረጃው አስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮች የተሳተፉበት ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም