በከተማዋ በተቀናጀ የኤች አይ ቪ/ኤድስ የመከላከል አገልግሎት ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል

87

አዳማ ነሐሴ 29 ቀን 2011 በአዲስ አበባ ከተማ በአዲሱ ዓመት የተቀናጀ የኤች አይ ቪ/ኤድስ የመከላከል አገልግሎት ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጥ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማድረስ ይሰራል።

የአስተዳደሩ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የእቅድ፣በጀትና ክትትል ቡድን መሪ አቶ ቴዎድሮስ ዘርጋው እንዳስታወቁት አገልግሎቱ ለቫይረሱ ተጋላጭና ልዩ ትኩረት የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመለየት ይከናወናል።

የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ከሚወሰዱ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች መካከል በሆነው አገልግሎት የባህሪ ለውጥ ተግባቦት ስራዎች እንደሚከናወኑም አስረድተዋል።

በአገልግሎቱ ከ700 ሺህ የሚበልበአፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣የሕግ ታራሚዎች፣መለዮ ለባሾችና ቫይረሱ በደማቸው የሚገኙ ወገኖችን ለመድረስ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በተለይ የመማማሪያ ማኑዋሎችንና የመረጃ ስርጸት መረጃዎችን በማዘጋጀትና በማሰራጨት የአቻ ለአቻና የሕይወት ክህሎት ትምህርት፣የወጣቶች፣የማህበረሰብና የሥራ ቦታ ውይይትን ጨምሮ ጥናትን መሠረት ያደረጉ ሕዝባዊ ኮንፈረንሶች ይካሄዳሉ።

መዋቅራዊ  ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል የገቢ ማስገኛ ፕሮግራም 25 ሺህ ለሚሆኑ ሴተኛ አዳሪዎችና ተጋላጭ ሴቶች፣ ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኝ ወገኖችና የትዳር አጋር የሌላቸው ሴቶች በማሰልጠን በገቢ ማስገኛ ስራዎች ለማሰማራት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

ለገቢ ማስገኛ የሚውሉ ግብዓቶት ለማቅረብ 15 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ለማሰባሰብ መታቀዱን አቶ ቴዎድሮስ አመልክተዋል።

በድጋፍና እንክብካቤ ረገድም ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኝ 16 ሺህ 358 ዜጎችና ወላጆቻቸውን በሞት ላጡ 36 ሺህ 507 ህፃናት የምግብና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ይደረጋል።

የበሽታውን ስርጭት ለመግታት 11 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ኮንዶም ለማሰራጨት የታቀደ ሲሆን፣ ከዚህም68 በመቶ የሚሆነው ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች ይሰራጫል ል።

ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለሚገኙና ከ557 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችንም በህይወት ክህሎት ስልጠና እንደሚሰጥ ቡድን መሪው አስታውቀዋል።

የኤች አይ ቪ ምክርና ምርመራ አገልግሎትን በማጠናከር 425 ሺህ የኅብረተሰብ ክፍሎች የደም ምርመራ ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመዲናዋ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ክትትል እየተደረገላቸው ካሉት 105 ሺህ ያህል ሰዎች 95 በመቶ የሚሆኑት የቫይረስ መጠናቸው ዝቅ እንዲል ይሰራል ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 ኤድስን የማቆም ራዕይ በማንገብ ግቦች ተቀርጸው በመተግበር ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ጽህፈት ቤቱ በያዝነው በጀት ዓመት ለሚያከናውኗቸው ስራዎች በአጠቃላይ 746 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙም ተመልክቷል።