ኢትዮጵያዊያን አዲሱን ዓመት ከቂምና ከበቀል በፀዳ መንፈስ እንዲቀበሉት አቡነ ማትያስ አሳሰቡ

79
ነሀሴ 29 /2011  (ኢዜአ)  "አዲሱን ዓመት ነጭ ለብሰን እንደምንቀበለው ሁሉ እኛም ውስጣችንን ከቂምና ከበቀል አጽድተን እንደ አዲሱ ዓመት አዲስ ሆነን መቀበል ይገባናል" ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘ ኢትዮጵያ አሳሰቡ። መጪው አዲስ ዓመት ቤተክርስቲያኒቱን ጨምሮ የመላው ኢትዮጵያ ችግሮች ይወገዱ ዘንድ ቤተክርስቲያን ፀሎት እንደምታደርግም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናግረዋል። ፓትሪያርኩ ይህንን የተናገሩት ዐራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዮስ  31ኛው በዓለ ሢመት በተከበረበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ነው። ፓትርያርኩ በዚህ ጊዜ "የአራተኛው ፓትርያርክ በዓለ ሢመት ከ20 ዓመታት የስደትና የመለያየት ጊዜ በኋላ በእናት ቤተክርስቲያን በመከበሩ ፈጣሪን እናመሰግናለን፣ ብፁዕነቶም እንኳን ደስ አሎት" ብለዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ በአሁኑ ወቅት አንድ ሆናለች ያሉት ፓትርያርኩ፤ በተለያየ ምክንያት ልዩነትን የሚሰብኩ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ የቤተክርስቲያኒቱ አንድነት ብዙ ሊማሩ ይገባል ሲሉም መክረዋል። "ቤተክርስቲያን ተለያይታ ነበር፤ በመለያየት የሚቀርብ ጸሎት ደግሞ በፈጣሪ ዘንድ አይደርስም፤ ለዚህም ምክንያቱ ፈጣሪ ተዋደዱ፤ አንድ ልቡና አንድ ቃል ሁናቹ ኑሩ ስለሚል ነው" ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው አንድነት ግን "ለፀሎታችን ስምረት ይሆነናል" ሲሉም ተናግረዋል። አዲሱ ዓመት አዲስ ሆኖ እንደሚመጣ ሁሉ መላው ህዝብ ከመለያየት፣ ከቂምና በቀል ውስጡን አጽድቶ በንፁህ መንፈስ ዓመቱን ሊቀበለው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት የሚከፋፍል ነገር በዚህ ጊዜ የሚነሳ አይደለም ያሉት ፓትርያርኩ፤ መለያየትን የሚሰብኩ ወገኖች ከስሜታዊነት ይፀዱ ዘንድ ማስተማርና መምከር ይገባልም ብለዋል። 31ኛው በዓለ ሢመታቸው እየተከበረ የሚገኘው ዐራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዮስ በተወካቸው በኩል መልዕክት አስተላለፈዋል። በዚሁ መልዕክታቸውም እግዚአብሔር ከሁሉ አስቀድሞ ለእኛ መልካሙን ሁሉ በማድረግ ጊዜ ሰጥቶ፣ ከቅድም ህልፈታችን በፊት የቤተ ክርስቲያንን ቅዱስ ሲኖዶስ አስተዳደር አንድ አድርጎ ስላሳየን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን ብለዋል። ኢትዮያዊያን በአንድ መንፈስ ሆነው ከግላዊ ፍላጎት በመታቀብ የተራራቁ እንዲቀራረቡ፣ የተራቡ እንዲጠግቡ፣ የታረዙ እንዲለብሱ፣ የተበደሉ ፍትህ እንዲያገኙ፣ የታሠሩ እንዲፈቱ በትጋት መጸለይ ይገባናል ሲሉ አሳስበዋል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ለህትመትና ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ይወጣ የነበረን አንድ ሚሊዮን ብር በመቆጠብ በተለያየ ምክንያት ለተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ማሠሪያ እንዲውል መስጠታቸውም በመረሐ ግብሩ ወቅት ተነግሯል። የአራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 31ኛው በዓለ ሢመት በመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት በሚገኘው ሰብከተ ወንጌል ዛሬ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም