በሸቀጣሸቀጥና እህል ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ ለችግር ተጋልጠናል---የበደሌ ከተማ ነዋሪዎች

50
መቱ (ኢዜአ) ነሀሴ 29 / 2011በበደሌ ከተማ በሸቀጣሸቀጥና እህል ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱ ለችግር እያጋለጣቸው መሆኑን  የከተማዋ ነዋሪዎች ገለፁ። ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እያካሄደ መሆኑን የቡኖ በደሌ ዞን ገበያ ልማት ፅህፈት ቤት አስታውቋል::አንዳንድ የበደሌ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ በጤፍ፣ ሽንኩርት፣ በዳቦ ዱቄት፣ በስጋ፣ በፓስታና መሰል ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል::የበደሌ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛ ወይዘሮ ትዕግስት ብርሀኑ እንዳሉት ከሁለት ወራት በፊት 2ሺህ 400 ብር የነበረው የአንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ ዋጋ በአሁኑ ወቅት 3ሺህ 200 ብር እየተሸጠ ነው:: አንድ ኪሎ ሽንኩርትም የ10 ብር ጭማሪ በማሳየት በ32 ብር እየተሸጠ መሆኑን ነው የገለፁት::" ከገቢዬ አንፃር የዋጋ ንረቱን መቋቋም አልቻልኩም" ያሉት ወይዘሮ ትዕግስት መንግስት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪውን በመቆጣጠር መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል:: በእንስሳት ዋጋ ላይ ጭማሪ ሳይኖር ልኳንዳ ቤቶች የአንድ ኪሎ ሥጋ ዋጋን በ60 ብር አሳድገው እስከ 220 ብር እንደሚሸጡ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ብሩ በቃና ናቸው። ከእህልና ሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች በተጨማሪም ከጥቂት ወራት በፊት 170 ብር የነበረው አንድ ኩንታል ስሚንቶ በአሁኑ ወቅት 420 ብር በመድረሱ መቸገራቸውን ተናግረዋል። በከተማው በጀበና ቡና ንግድ ሥራ የተሰማሩት ወይዘሮ ነፃነት አባተ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ነጋዴዎች እርስ በእርስ ተነጋግረው በሁሉም የእህል ምርቶች ላይ እንደፈለጉ ዋጋ በመጨመር ለችግር እያጋለጧቸው መሆኑን ገልፀዋል። በከተማው በሽንኩርት ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ አንዋር ሲራጅ እንዳሉት የሽንኩርት ምርቱን ከሚያመጡበት ወሊሶ እና ባቱ አካባቢዎች ዋጋው በመጨመሩ የዋጋ ለውጥ መኖሩን ተናግረዋል። የሽንኩርት ምርት በሚወጣበት ጊዜ እና ገበያ ላይ ምርት ሲበዛ ዋጋው ሊቀንስ እንደሚችልም ጠቁመዋል። በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በቡኖ በደሌ ዞን ገበያ ልማት ፅህፈት ቤት የገበያ ልማት ቡድን መሪ አቶ ጅብሪል ሰይድ እንዳሉት በዞኑ 9 ወረዳዎችና በበደሌ ከተማ የገበያ ክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተካሄደ ነው:: ባለፉት ሁለት ወራት በ4ሺህ 246 የንግድ ተቋማት ላይ በተደረገው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ 549 የሚሆኑት ተቋማት ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ አድርገው መገኘታቸውን ገልጸዋል። "ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ካደረጉት ከእነዚህ የንግድ ተቋማት 122 የሚሆኑት ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው በመሆኑ እንዲታሸጉ" ተደርጓል። ቀሪዎቹ በተገቢ ዋጋ እንዲሸጡ በማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን አመልክተዋል:: በአካባቢ ገበያ ላይ በሚፈጠር እጥረትና በመሀል ደላሎች መበራከት የሚከሰተውን የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር የቡኖ እና ሰዴተን ጮራ ዩኒየኖች ምርት በማስመጣት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያከፋፍሉ ከስምምነት መደረሱንም አቶ ጅብሪል አስረድተዋል። ባለፉት ሁለት ሳምንታት 380 ኩንታል ጤፍ እና 240 ኩንታል ዱቄት በማስምጣት በተመጣጣኝ ዋጋ እየተከፋፈለ መሆኑንም ተናግረዋል::    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም