ሕጻናት ተፈጥሮን እንዲንከባከቡ ወላጆች ሊያግዟቸው ይገባል-የቀድሞ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ

52
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 ሕጻናት የአካባቢ ጥበቃና የችግኝ መትከል ባሕል እንዲያጎለብቱ ወላጆች ሊያግዟቸው እንደሚገባ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ርእስ ብሔር ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ አሳሰቡ። እድሜያቸው ከ 7 እስከ 12 ዓመት የሚሆኑ ከሰባት ትምህርት ቤት የተውጣጡ ሕጻናት በዛሬው እለት በቀደሞው ፕሬዝዳንት  ቅጥር  ግቢ በመገኘት ችግኞችን ተክለዋል። አቶ ግርማ በዚህ ወቅት እንዳሉት ልጆችን ገና በለጋ እድሜያቸው የአካባቢ ጥበቃ ላይ እንዲያተኩሩ፣ ከተፈጥሮ ጋር ቅርርብ እንዲፈጥሩና ዛፎችን በመትከል መንከባከብ የሚያስችላቸውን ባሕል እንዲያዳብሩ ማገዝ ያስፈልጋል። ይህንን ተግባር በልጆች ማንነት ውስጥ ባሕል ለማድረግ እንዲቻልም ወላጆችና የልጆች አሳዳጊዎች ሕጻናትን ማስተማርና ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። "ዛሬ ልጆች በለጋ እድሜያቸው የሚተክሉት ዛፍ አእምሯቸው ውስጥ ነው የሚያድገው" ያሉት አቶ ግርማ፤ ወደ ፊት የምትፈጠረውን አረንጓዴ ኢትዮጵያ በሕጻናት ጉልሕ አስተዋጽኦ ማልማት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የህጻናት መጽሐፍ ያዘጋጀው አቶ ጥበበ አክሊሉ፤ 'አባባ ዛፉ' በሚል ፕሮጀክት 'አንድ ሕጻን አንድ ዛፍ' በሚል መሪ ሀሳብ ሕጻናት ዛፎችን መትከልና መንከባከብን ባሕል እንዲያደርጉ እየሰራ ይገኛል። ዓለም አቀፍ የሙቀት መጨመርና የአየር ብክለትን ለመከላከል ይቻል ዘንድም ሁሉም ሰው ዛፍ መትከል እንዳለበት ጠቁሞ፤ በርካታ ሕጻናት ችግኝ እንዲተክሉ ቢደረግ ሀገሪቷን አረንጓዴ ማድርግ ይቻላል ብሏል። ልጆች ችግኞችን መትከል እየተለማመዱ ካደጉ "ዛፎችን አይቆርጡም" ያለው አቶ ጥበበ፤ ልጆች በራሳቸው ችግኞችን ተክለው እንዲያሳድጓቸውና እንዲንከባከቧቸው ወላጆች ትልቅ ሚና መጫወትና ማበረታታት እንዳለባቸውም አስገንዝቧል። 'አባባ ዛፉ' ፕሮጀክት በክረምት ወራት በርከት ያሉ ሕጻናት በስማቸው ችግኞችን ተክለው እንዲንከባከቡና እንዲያለሙ የማድረግ አላማ እንዳለውም አስረድተዋል። ከካቦድ ትምሕርት ቤት ሕጻናት ልጆችን ዛፍ እንዲተክሉ ይዘው የመጡት ወይዘሮ መና ዳታን "ልጆች የጓሮ አትክልትን መንከባከብ፣ አበቦችን እንዲያለሙና ተፈጥሮ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲያደርጉ መስራት አስፈላጊ ነው" ይላሉ። የአካባቢያችን አየር እንዳይበከልና ወደ ፊት የተሻለ የአየር ንብረት እንዲኖረን ካስፈለገም "ዛሬ ላይ ልጆች ዛፍ የሚተክሉና የሚንከባከቡ እንዲሆኑ ለማድረግ ማስተማርና የተፈጥሮ እንክብካቤን ማለማመድ ከወላጆች ይጠበቃል ነው" ያሉት ወይዘሮ መና። ልጆች ገና በለጋ እድሜያቸው ተፈጥሮን በስስትና በጥንቃቄ መያዝን እንዲለምዱት ለማድረግ መምህራንና ወላጆችም ሊያግዟቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ወይዘሮ መና ልጆች በትምህርት ቤታቸው በቀላል ቁሳቁሶች አበቦችና ቀላል ችግኞችን ተክለው ጠዋት ማታ ሲገቡና ሲወጡ ወኃ በማጠጣት እንዲያሳድጉና እንክብካቤ እንዲያደርጉ እየተደረገ መሆኑንም  ተናግረዋል። ይሕ አካሄድ በሌሎች በርካታ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶችና በመኖሪያ ቤታቸው ተግባራዊ ቢደረግ የተሻለ ለተፈጥሮ የሚቆረቆር ትውልድና ለምለም አካባቢን መፍጠር ይቻላል ይላሉ ወይዘሮ መና ። ከሻምፒዮንስ አካዳሚ ዛፍ ለመትከል የመጣው ሕጻን ያቤጽ ሹምዬ "በረሃማነትን ለመቀነስና ኢትዮጵያና አፍሪካን  አረንጓዴ ለማድረግ ዛፎችን ተክሎ ማሳደግ አስፈላጊ መፍትሔ ነው" ይላል። ዛሬ የተከላቸው ችግኞችን  በሌላ ጊዜ እየተመላለሰ እንደሚንከባበብ የገለጸው ሕጻን ያቤጽ፣ ሕጻናት ችግኞችን ተክለው ውኃ እያጠጡና እየኮተኮቱ  ዛፍ እስኪሆኑ ድረስ መንከባከብ አለባቸው ሲልም አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም