ለችግረኛ ተማሪዎች ከ650 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

68
አምቦ፣ አሶሳ ፣ ነቀምቴ   ነሃሴ 28 /2011 --- በወሊሶና አሶሳ ከቶሞች እንዲሁም በአገሎ ወረዳ ለሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎች ግምታቸው ከ650 ሺህ ብር በላይ የሆኑ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ። በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የወሊሶ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገው በከተማው ለሚገኙ 370 ችግረኛ ተማሪዎች ነው። ለተማሪዎቹ የተበረከተው ድጋፍ ከ300 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል። የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ሀብታሙ ኃይሌ ለኢዜአ እንደገለጹት ለተማሪዎቹ በድጋፍ የተሰጡት ደብተሮች፣ እስክርቢቶዎችና ቦርሳዎች ሲሆኑ ከ300 ሺህ ብር በላይ ግምት አላቻው።” ለችግረኛ ተማሪዎች ድጋፉን ያደረገው “ወሊሶ ለወሊሶ” የተባለ ማህበር መሆኑንም አመልክተዋል። “ማህበሩ በከተማው ችግረኛ ተማሪዎችን በመርዳት ላይ ይገኛል” ሲሉም ጠቁመዋል፡፡ ድጋፍ ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሒሩት አለማየሁ በሰጠችው አስተያየት ቤተሰቦቿ የገቢ አቅማቸው ደካማ በመሆኑ በየዓመቱ የትምህርት ቁሳቁስ ለማግኘት ትቸገር ነበር። ማህበሩ ያደረገላት የትምህርት ድጋፍ በየዓመቱ ያጋጥማት የነበረውን የትምህርት ግብዓት ችግር እንደፈታላትም ተናግራለች። ተማሪ አበባየሁ ፈጠነ በበኩሏ “የተደረገልኝ የደብተርና የእስክርቢቶ ድጋፍ ትምህርቴን በአግባቡ እንድከታተል ይረዳኛል፤ በየዓመቱም ከማህበሩ ድጋፍ አገኛለሁ ” ብላለች ። የወሊሶ ለወሊሶ ማህበር ሊቀመንበር አቶ አለማሁ ታረቀኝ በበኩላቸው እንዳሉት ተማሪዎች በመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ በማሰብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል። በተያያዘ ዜና በአሶሳ ከተማ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰበሰበ 270 ሺህ ብር የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ ለችግረኛ ህጻናትና ቤተሰቦች ተከፋፍሏል። በምስራቅ ወለጋ ዞን ዋማ አገሎ ወረዳም ለችግረኛ ሕጽናትና አቅም የሌላቸው ነዋሪዎች መሰል የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ የወረዳው ሴቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው ድጋፉ የተደረገው በዜግነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም