ፍቼ ጫምባላላ ባህላዊ ቅርስነቱን ጠብቆ ለማቆየት የሚጠበቅብንን እንወጣለን ---ወጣቶች

128
ሃዋሳ ሰኔ7/2010 አባቶችና እናቶች ጠብቀው ለትውልድ ያስተላለፉትን የሲዳማ ዘመን መለወጫ /ፍቼ ጫምባላላ/ ባህላዊ ቅርስን ጠብቀው ለማቆየት በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ገለፁ፡፡ ወጣት ሚላ ፍስሃ ባህሉ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በዓል በመሆኑ ይዘቱን በመጠበቅና በተረጋጋ መንገድ ማክበር ይገባል ብላለች፡፡ ፍቼ ጫምበላላ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ የአለም ቅርስነት መመዝገቡ  ለዞኑ፣ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ  ኩራት መሆኑን ተናግራለች፡፡ ባህላዊ ስርዓቱን  ጠብቆ ቅርሱ በውስጡ የያዛቸውን እሴቶች በማወቅ ማክበር እንደሚያስፈልግ ገልጻለች፡፡ ''ወግና ስርዓቱን ማክበር አለብን'' ያለቸው ወጣት ሚላ ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን በሰከነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንዳለባቸው ጠቁማለች፡፡ "አባቶች ጠብቀው ያቆዩልንን የፍቼ ጫምባላላን ዘመን መለወጫ በዓል የአከባበር ስርዓቱ በሚጠይቀው ሁኔታ ብቻ ማሳለፍ ያስፈልጋል" ያለው ደግሞ በበዓሉ የታደመው ወጣት ተመስገን ብርሃኑ ነው፡፡ ወጣቶች በስሜታዊነት ካልተገቡ ተግባራት በመቆጠብ  በሰከነ መንገድ በዓላትን ማክበር እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡ ''በጫምባላላ እለት በሚከናወነው የቄጣላ ስርዓት ውስጥም አላስፈላግ ነገር መቀላቀል አይገባም ሲል'' ተናግሯል፡፡ ወጣት ሚሊዮን መንገሻ በበኩሉ ''አባቶች ጠብቀው ያስረከቡንን ይህንኑ በዓል ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ በማክበር የባህሉንና የክልሉን ገፅታ ለመገንባት ኃላፊነት  ወስደን መስራት ይኖርብናል'' ብሏል፡፡ ''በዓሉ የፖሊቲካ፣ የኢኮኖሚና ሌሎች ማህበራዊ ጥያቄዎች የሚንፀባረቁበት ሳይሆን የእርቅ፣ የአንድነት፣ የሰላምና የነፃነት ነው''  ያለው ደግሞ ወጣት ሽመልስ ዱሬሳ ነው፡፡ ''ወጣቶች ስለፊቼ የተፃፉ መጻህፍትና ሰነዶችን አንብበን በማወቅና ከስሜታዊነት መንፈስ ወጥተን የአለም ቅርስ የሆነውን ጫምባላላን ጠብቀን ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት ይኖርብናል'' ብሏል ፡፡ የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ ፍቼ በዓል ለተከታታይ 15 ቀናት በዞኑ ባሉ ወረዳዎች እንደሚከበር ታውቋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም