በኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ ይፈጠራል

112
አዳማ ነሐሴ 27 / 2011 በኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ገለጸ። የክልሉ ዓመታዊ የኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል። በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ ዜጎችን የሥራ ባለቤት እንዲሆኑ የተቀናጀ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ነው። ለዕቅዱ ስኬታማነት የክልሉ መንግሥት ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር ማዘጋጀቱን አስረድተዋል። ዜጎችን ከሥራ አጥነት ማውጣት የክልሉ መንግሥት ''ቁልፍ ተግባር'' መሆኑንም ዶክተር ግርማ አመልክተዋል። ሥራ ከሚፈጠርባቸው ዘርፎች መካከል ግብርና ፣ማኑፋክቸሪንግ ፣ግንባታ፣ አገልግሎት ፣ የእንስሳት እርባታና ንግድ ይገኙበታል ብለዋል። ሥራ  ከሚፈጠርላቸው ዜጎች መካከል 37 በመቶ የሚሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ይሆናሉ።የሴቶችን ተሳትፎ 50 ከመቶ ለማድረስ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም ተናግረዋል። የክልሉ ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻ በበኩላቸው ዕቅዱን ስኬታማ ለማድረግ ለኢንተርፕይዞች ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል። በተጨማሪም የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ በአቅም ግንባታ ፣ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ልማት የማደራጀትና የማብቃት ሥራ ይከናወናል ብለዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ670 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሥራ መፈጠሩንና ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ብድር መሰራጨቱን አመልክተዋል። ይህም ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለማሰራጨት ከተያዘው ዕቅድ አንጻር አፈጻጸሙ 34 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል። ለእቅዱ አፈጻጸም ዝቅተኛነት የቅንጅታዊ አሰራር ክፍተት ፣ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ማነስ ፣ የበጀት ስርጭትና አቅርቦት በሚፈለገው መልኩ አለመሆን ፣ የአመለካከትና የፀጥታ ሁኔታ በምክንያትነት ጠቅሰዋል። ጅማ ፣ ሰሜንና ምስራቅ ሸዋ፣ አርሲ፣ ምዕራብ አርሲና ኢሉአባቦር የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ዞኖች እንደነበራቸው ኃላፊው አመልክተዋል። ከከተሞች አዳማ ፣ሻሸመኔ ፣ ቡራዩ ለገጣፎ ፣ ባቱ ፣ ገላን ፣ ጅማና ቢሻን ጉራቻ መልካም አፈጻጸም እንደታየባቸው ተናግረዋል። በመድረኩ ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና ከተሞች የተውጣጡ ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም