በስራቸው እድገት ማስመዝገባቸውን በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችና ግብዓት አቅራቢዎች አስታወቁ

52
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 በስራቸው እድገት ማስመዝገባቸውን በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችና ግብዓት አቅራቢዎች አስታወቁ። እየተካሄደ የሚገኘው የ2ኛው ዙር ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክሪንግ ኢንዱስትሪ ኤግዚቢሽንና ባዛር ተሳታፊዎች እንደገለፁት ባስመዘገቡት ውጤት የደረጃ ሽግግር ማድረግ ችለዋል። በአክሎግ ጄኔራል ትሬዲንግ ኩባንያ የማርኬቲንግ ሶሉሽንና ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ሩቅነህ አደመ እንደተናገሩት "ኩባንያው ከ7 ዓመታት በፊት ሲቋቋም ለዱቄት ፋብሪካዎች የሚሆን መለዋወጫዎችን ብቻ ያቀርብ ነበር"። በጊዜ ሂደት ትላልቅ መሳሪያዎችን ለአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ  ኢንዱስትሪዎች በማቅረብ ስራውን አያሳደገ በመምጣቱ ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ደረጃ ማደጉን ገልፀዋል። የድርጅቱ የካፒታል መጠንም ከአነስተኛ ገንዘብ ተነስቶ አሁን በሚሊዮን የሚቆጠር ሆኗል ብለዋል። ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ከ1 መቶ በላይ ሰራተኞች እንዳሉት የጠቆሙት አቶ ሩቅነህ፤ በቀጣይም የመለዋወጫ እቃዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ እንደሚያቋቁሙ ተናግረዋል። "የመገጣጠሚያ ፋብሪካው ሲቋቋም ከ300 በላይ ሰራተኞች ይኖረዋል" ያሉት አቶ ሩቅነህ፤ ኩባንያው ከ7 ዓመታት በፊት ሲቋቋም የገበያ ትስስር፣ የእውቀት ክፍተትና የጥሬ እቃዎች ችግር እንደነበሩበትም ገልፀዋል። በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ለመሳተፍ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የመጡት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች መካከል ወይዘሮ ይፍቱስራ ገብረጻድቅ በበኩላቸው ከጥቃቅን የባህል ሽመና ተነስተው አሁን መካከለኛ የማምረት ዘርፍ ኢንዱስትሪ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። "መንግስት ያደረገልን ድጋፍና እኛም ባደረግነው ጥረት በማሽን የሚፈተል ጥጥን በመጠቀም የጨርቃ ጨርቅና የባህል አልባሳት አምራች ፋብሪካ በማምረት የካፒታል መጠናችን ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችለናል" ብለዋል። በቅርቡ ፋብሪካውን ለማሳደግ መታቀዱን የጠቆሙት ወይዘሮ ይፍቱስራ፤ የድርጅቱ ሰራተኞች ቁጥር አሁን ካለበት 18 እንደሚጨምርም ለኢዜአ ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በአነስተኛና ጥቃቅን በመደራጀት ስራ ጀምረው አሁን ወደ መካከለኛ የማምረት ዘርፍ ኢንዱስትሪ በመሸጋገራቸው ማሽኖችን መግዛታቸውን የተናገሩት ደግሞ ከቡራዩ ከተማ የመጡት የጨርቃ ጨርቅ ድርጅት ባለቤቶች ናቸው። ከድርጅቱ ባለቤቶች መካከል ሰላማዊት ሁሴን እንደተናገሩት  የካፒታል መጠናቸው  ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል። "በመካከለኛ ዘርፍ አምራች ኢንዱስትሪ ደረጃ ስራችን ስንቀጥል የሰራተኞች ቁጥር አሁን ካለበት 8 ሰው ከአምስት እጥፍ በላይ ይጨምራልም" ብለዋል። የጥሬ እቃዎችና የገበያ ትስስር ችግር መኖሩ በአነስተኛና ጥቃቅን ደረጃ ብቻ ሽግግር ሳናደርግ እንድንቆይ ምክንያት ሆኗልም ብለዋል። "በተለይም ምርቶቻችንን  በጅምላ ለመሸጥ የሚያስችል ሀገር አቀፍ ሰፊ የገበያ እድል አለመኖሩ እና ወቅትን ብቻ ጠብቀን እንድንሸጥ መገደዳችን ሌላ ችግር ሆኖብን እንድንቆይ አድርጎናል" ብለዋል። በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ የሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የደረጃ ሽግግር እንዲያደርጉ  መንግስት ከባለቤቶቹ ባልተናነሰ መልኩ የጥሬ እቃ፣ የእውቀት፣ የቦታና የገበያ ትስስር ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንዳለበትም ሌሎች የኤግዚቢሽንና ባዘሩ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም