ተማሪዎች በካርቶን ተሸፍነው እንዲፈተኑ ያደረገው መምህር እያነጋገረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ተማሪዎች በካርቶን ተሸፍነው እንዲፈተኑ ያደረገው መምህር እያነጋገረ ነው
66
ነሐሴ 27/2011 ኩረጃን ለማስቀረት ተማሪዎች በካርቶን ተሸፍነው እንዲፈተኑ ያደረገው መምህር በርካቶችን እያነጋገረ ነው። ሰሞኑን በሀገረ ሜክሲኮ የሆነው ነገር ብዙዎችን አስገርሟል፤ አነጋግሯል። በትላክሳላ ክልል በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ፥ ተማሪዎች ለፈተና ተቀምጠዋል። መምህር ሊዊስ ሁዋሬዝ ቴክሲስ ተማሪዎቻቸው ፈተናውን እንዳይኮራረጁ በማሰብ ጭንቅላታቸው ላይ በካርቶን እንዲሸፈኑ አድርገዋል። ይህን የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ የትስስር ገጾች ተሰራጭቶ በርካቶችን አነጋግሯል። ጉዳዩን የሰሙት የተማሪዎች ቤተሰቦችም በሁኔታው ብስጭታቸውን በመግለፅ፤ መምህሩ የልጆቻቸውን ሰብዓዊ መብት በመጣስ ያልተገባ ድርጊት ስለፈፀሙ እንዲባረሩ ጠይቀዋል። በአንጻሩ በማህበራዊ የትስስር ገጽ እስቻውን እና በካርቶን የተሸፈኑ ተማሪዎችን የፈተና ሁኔታ የሚያሳየው ምስል በተሰራጨበት ወቅት ድርጊቱን ያደነቁም አሉ። መምህሩን ተማሪዎች እንዳይኮራረጁ የተጠቀምከው መንገድ አሪፍ ስለሆነ እናደንቅሃለን የሚሉም አልጠፉም። ስለሁኔታው በጋዜጠኞች የተጠየቁት መምህር ቴክሲስ በበኩላቸው፤በክፍሉ ውስጥ ያለውን የፈተና ሂደት ለመታዘብ ብቻ እንደተገኙ ተናግረዋል። ሆኖም ኩረጃን ለመከላከል በካርቶን ተሸፍኖ መፈተንን በተመለከተ ተማሪዎቹ ፈቅደውና ተስማምተው እንደተተገበረ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም በ2013 በሀገረ ታይላንድ ኩረጃን ለመከላከል ሲባል ተማሪዎች ከወረቀት የተሰሩ የጎን ዕይታን የሚሸፍኑ ሄልሜቶችን ለብሰው መፈተናቸው ይታወሳል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው አትቷል።