ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም የድርሻውን እንደሚወጣ የቀድሞ ሰራዊት በጎ አድራጎት ማህበር ገለጸ

49
ጎንደር ኢዜአ ነሃሴ 26/2011 ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትና ሰላም መከበር የድርሻውን እንደሚወጣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚገኘው የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት በጎ አድራጎት ማህበር ገለፀ፡፡ በጎንደር ከተማ ዛሬ የማህበሩ አንደኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ከ3ሺህ አምስት መቶ በላይ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ውይይት ተካሄዷል፡፡ የማህበሩ ሊቀመንበር ሻምበል ዮሴፍ ደመቀ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የህይወት ልምዳቸውን በመጠቀም የህዝቡን አንድነትና አብሮነት የሚሸረሽሩ እንቅስቃሴዎችን ለማክሸፍ እያገዙ ነው፡፡ ማህበሩ ሲመሰረት የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት አባላት በሀገራቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ተሳታፊ እንዲሆኑ በሰላምና ዴሞክራሲያዊ ጉዞውም የራሳቸውን አሻራ እንዲያስቀምጡ ዓላማ ይዞ መሆኑን ገልጸዋል። አባላቱ በልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ተሳታፊ በመሆን በህዝቦች መካከል ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ ኢትዮጵያዊ ስብዕናና አብሮነትን ለማጠናከር የድርሻውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የዘረኝነትና ጎጠኝነት አስተሳሰብን ከመቃወም አልፎ እንፀየፋለን፤›› ያሉት ሊቀመንበሩ ሁሉም የማህበሩ አባላትና ቤተሰቦቻቸው አብሮ የመኖርና የመልማት እሴቶችን እንዲጠብቁ የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሊቀመንበሩ እንዳሉት ማህበሩ በአካባቢው ሰላምና ልማት ላይ በመሳተፍ ግጭቶች እንዲወገዱና የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ በማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በዞኑ በነበረው አለመረጋጋት ከመንግስትና ከሌሎች በጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመሆን ሰላሙ እንዲመለስ፣  በጎንደር ከተማ በሚከበሩ ህዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት ላይም ፀጥታ ማስከበር ላይ መስራታቸውን ጠቅሰዋል። በልማቱ በኩልም የማህበሩ አባላት በጉልበትና በገንዘብ ተሳታፊ መሆናቸውንና በሀገር አቀፍ ደረጃ ለነበረው የአረንጓዴ አሻራ ቀን ከ8 ሺህ በላይ ችግኞች መትከላቸውንም  አመላክተዋል፡፡ የማህበሩ አባል የመቶ አለቃ ደሴ ምትኩ በበኩላቸው ‹‹ልዩነትን በማክበር ለሀገር ግንባታና እድገት በጋራ መቆም ይገባል›› ብለዋል፡፡ በመድረኩ በእንግድነት የተገኙት የጎንደር ከተማ ከንቲባ የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ ተሾመ አድማሱ ማህበሩ አሁን ያለውን ለውጥ ዳር ለማድረስ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም አብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ "ከማህበሩ አባላት የኢትዮጵያዊነት ስሜትና የልማት አስተሳሰብም መላ ህዝቡ ትምህርት ሊወስድ ይገባልም "ብለዋል፡፡ ማህበሩ ከ4 ሺህ 400 በላይ አባላት ያሉት ሲሆን በቀጣይም በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ድጋፍ እንደሚደረግም ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም