ኢትዮጵያ የቱርክ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በአገሪቷ የበለጠ እንድያፈሱ ትሰራለች -አምባሳደር አያሌው ጎበዜ

74
አዲስ አበባ ሰኔ7/2010 የቱርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን በስፋት እንዲያፈሱ አገሪቷ ጠንክራ እንደምትሰራ በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር አያሌው ጎበዜ ገለጹ። አምባሳደር አያሌው 'ዴይሊ ሳባ' ከተባለ የቱርክ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የቱርክ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ይበልጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ አገሪቷ ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ባደረሰው መረጃ አስታውቋል። ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የሁለቱ አገራት ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት በፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል አምባሳደሩ። በኢትዮጵያ ያለው የቱርክ ኢንቨስትመንት ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰም ተጠቁሟል። በሌላ በኩል አምባሳደር አያሌው ጎበዜ በቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር አህመት ሪዛ ድሚሬር ጋር ተወያይተዋል። አምባሳደሩ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ በቅርቡ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ለአምባሳደር አህመት ሪዛ ድሚሬር ማብራራታቸውን የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያና ቱርክ ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ አገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1896 ነው። የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ኢትዮጵያን ሶስት ጊዜ መጎብኘታቸው ይታወቃል። በኢትዮጵያ ከ165 በላይ የቱርክ ኩባንያዎች መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ለ30 ሺህ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል የፈጠሩ ሲሆን፤ በአጠቃላይ አገሪቷ በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በዋነኝነት ከሚጠቀሱ አገራት መካከል ትካተታለች።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም