ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማነት በጋራ መረባረብ አለብን ---ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

108
ነሐሴ 25/ 2011 " የኢንዱስትሪ ሰላምና ውጤታማነት መረጋገጥ በጋራ መረባረብ አለብን " የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አሳሰቡ። ሚኒስቴሩ "ሰላም፣ይቅርታና ፍቅር ለጠንከራ ማህበራዊ ትስስርና ለመልካም የኢንዱስትሪ ግንኙነት " በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው 16ኛውን የፌዴራልና የክልሎች የሴክተር ተቋማት ጉባኤ ዛሬ  በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በጉባኤው መክፈቻ ስነስርዓት ሚኒስትሯ እንደገለጹት የኢንዱስትሪ ሰላምን ማረጋገጥ ብቻውን ልማትና ዕድገት አያመጣም። "በኢንዱስትሪው ዘርፍ የገበያ ውድድርና የሥራ ሥምሪት ውጤታማነት እውን በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚቻልበት ሂደት ላይ መረባረብ ይጠበቅብናል "ብለዋል። ለዜጎች ማህበራዊ ደህንነት ፖሊሲ ተግባራዊነት በትብብር ከተሰራ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሰላምን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርታማነትን በማሳደግ በሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና መጫወት እንደሚቻል ገልጸዋል። የዜጎች የአኗኗር ዘይቤ እንዲለወጥና ሁሉም በእኩል ተጠቃሚ እንዲሆን በዘርፍ የወጡ አዋጆች፣የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮችን በተጨባጭ ወደ መሬት ማውረድ እንደሚገባም አስገዝበዋል። "የሥራ ቦታ ደህንነት ለማረጋገጥና የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ ሀገራዊ አቅም በመፍጠር ላይ ትኩረት አድርገናል "ያሉት ሚኒስትሯ ሠራተኛው በሰለጠነ መንገድ መብትና ጥቅሙን እንዲያስከብር ማገዝ  እንደሚገባም አመልክተዋል። የሥራ ገበያን መረጃ በማደረጃት፣በማመንጨትና በማሰራጨት በኩል በዘርፉ ያገጠሙን ክፍተቶች እንደሆኑ ጠቁመው የህንን ችግር በመፍታት ፈጣን  እድገት ውስጥ መግባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የሰመረ የአሰሪና ሠራተኞች ግንኝነት ማረጋገጥ ለኢንዱስትሪ ሴክተር ምርታማነትና እድገት ሚናው የላቀ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሌ ናቸው። በሁሉም የውጭና የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች የሠራተኞች መደራጀት ችግር እየሆነ መምጣቱን አመልክተው ችግሩ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ጭምር እንደሚስተዋል ተናግረዋል። "ሰላማዊ ጥያቄ ወደ አመፅና ሁከት ከተቀየረ አሁን ያለው የኢንዱስትሪ ሰላምና ደህንነት ከመናጋቱም በላይ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያሳድራል "ብለዋል። መንግስት ችግሩን ለመፍታት የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቢያሻሽልም የአፈፃፀም መመሪያዎች በተገቢው ሥራ ላይ እየዋሉ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ችግሩን ለማስወገድ መንግስት፣ባለድርሻ አካላትና የኢንዱስትሪው ዘርፍ  ለጋራ ተጠቃሚነት በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን በበኩላቸው የኢንዱስትሪዎች ሰላምና ደህንነት የሚረጋገጠው በዘርፉ የጋራ ተጠቃሚነት ሲኖር  በመሆኑ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊዋ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። ጉባኤው የተጠናቀቀው በጀት ዓመት  የሥራ ክንውንና የተያዘው የስራ ዘመን ሀገራዊ መነሻ እቅድ ላይ በመምከር የጋራ የማስፈፀሚያ ስልትና አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም