በኢትዮጵያ የተፈጠረው የሚዲያ ነፃነት ለዘርፉ መስፋፋት ጉልህ ሚና ቢኖረውም ሙያተኛው ግን በአግባቡ እየተጠቀመበት አይደለም ተባለ

103
ነሀሴ 25/2011 በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን የሚዲያ ነፃነት የዘርፉ ባለሙያዎች በአግባቡ እየተጠቀሙበት አይደለም ሲሉ ምሁራን ገለፁ። የግል መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው የፖለቲካ ለውጡን ተከትሎ እየተስፋፋ የነበረው የመረጃ ተደራሽነት ተመልሶ እየጠበበ መምጣቱን ይናገራሉ። በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ሁለንተናዊ የለውጥ ሂደት ካመጣቸው ትሩፋቶች መካከል የመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚስተዋለው የሥራ ነፃነት አንዱ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ። መንግስት ባልተለመደ ሁኔታ የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን አመቺ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር የመረጃ ምንጭ አማራጮችም እንዲሰፉ የበኩሉን ተግባር ማከናወኑንም እንዲሁ። ለዚህም ማሳያው መስራት ተስኗቸው ከአገር የወጡ ጋዜጠኞች ወደአገር ቤት ተመልሰዋል፤ በአገር ውስጥም ተዘግተው የነበሩ የህትመት ሚዲያዎች ሥራቸውን ጀምረዋል ሲሉም ያመለክታሉ። ከዚህም በተጨማሪ ከዚህ በፊት ለሚዲያ ተቋማት ዝግ የነበሩ የመንግስትና ሌሎች መረጃዎችም በተሻለ መጠን ለመገናኛ ብዙሃን ክፍት መሆናቸውንም የዘርፉ ባለሙያዎችና ምሁራን ይገልፃሉ። ይሁን እንጂ የመገናኛ ብዙሃኑ የተፈጠረላቸውን ይህንን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ እየተጠቀሙበት አይደለም ሲሉ ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ምሁር የሆኑት ዶክተር ንጉሴ ተፈራ ይናገራሉ። ከለውጡ በፊት 'አድርጉ አታድርጉ' የሚለው ልዩነትና ግጭት በመንግስትና በመገናኛ ብዙሃኑ መካከል እንደነበር የሚገልፁት ዶክተር ንጉሴ ነፃነቱ ከመጣ በኋላ ግን ልዩነቱና ግጭቱ በህዝቡና በመገናኛ ብዙሃኑ መካከል እየሆነ ነው ሲሉም አመልክተዋል። ለዚህም ምክንያቱ አብዛኛው የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኛ ሥራውን እያከናወነ ያለው ከሙያው ስነ ምግባርና መርሆ ባፈነገጠ መንገድ መሆኑ ነው በማለት ተናግረዋል። ዶክተር ንጉሴ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ህዝቡ የሚፈልገውንና የሚመጥነውን መረጃ እያቀረቡ አይደለም። የግሉ የመገናኛ ብዙሃን አካላት በበኩላቸው መንግስት በለውጡ መጀመሪያ አካባቢ የመረጃ ተደራሽነትን ለማስፋት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ መልሶ እያጠበበው ነው ሲሉ ይወቅሳሉ። የማስታወቂያ ፍትሃዊ ስርጭት አለመኖር በግሉ ዘርፍ ላይ የአቅምና የመረጃ ውስንነት እንዲመጣ እያደረገ መሆኑንም እንዲሁ። ይህም የመገናኛ ብዙሃኑ ህልውናቸውን ለማስቀጠል ሌላ አማራጭን እንዲከተሉ እያደረጋቸው ነው በማለት ይገልፃሉ። ለዚህም ሲሉ የመገናኛ ብዙሃኑ አገራዊ መረጃዎችን ከማቅረብ ይልቅ ገንዘብ ተኮር ወደሆኑት የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ለማተኮር እየተደዱ እንደሆነም አክለዋል። ከዚህም ባሻገር በአሁኑ ወቅት ካለው አገራዊ የፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ የለውጥ ሂደት ጋር የተያያዙ የመገናኛ ብዙሃን የትንታኔ ዘገባዎችን ለማቅረብ ጥልቅ የሆነ የሙያ ክህሎት ያስፈልጋል የሚሉት የመገናኛ ብዙሃኑ አባላት የአንዳንድ የግል መገናኛ ብዙሃን ባለቤቶች ግን በዘርፉ ልምድ ያላቸው አይደሉም፤ ይህም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለአገርና ህዝብ የሚፈይድ ተግባር ለመከወን እንቅፋት እየሆነ ነውም ይላሉ።         የመገናኛ ብዙሃኑ ያላቸውን አቅም፤ ጋዜጠኛውም የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን ተረድተው ሃላፊነትና ተጠቀያቂነት ባለው መንገድ ሊሰሩ እንደሚገባም የዘርፉ ምሁራን አሳስበዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም