ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨሲቲ ከ100 ማህበረሰብ ተኮር የምርምር ኘሮጀክቶችን እያካሔደ ነው

49
የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ  ከአንድ መቶ በላይ ማህበረሰብ ተኮር የምርምር ፕሮጄክቶች በማካሄድ ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡ በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ተመስገን ተረፈ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም የአካባቢውን ህብረተሰብ ችግር የሚፈቱ የተለያዩ ምርምሮችን እያደረገ ይገኛል። በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሚካሄዱ ምርምሮች  በግብርና፣ በትምህርት ጥራት፣ በተፈጥሮ ሀብት አካባቢ ጥበቃና ሌሎች ችግር ፈቺ ኘሮጀክቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ውስጥ የሚገኙ በተደጋጋሚ በጎርፍ በሚጠቁ ከተሞች ዙርያም ጥናት እያደረገ እንደሚገኝና ለምርምር ስራዎቹ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን አስታውቀዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የተከናወኑትን ከ36 በላይ የምርምር ውጤቶች እውቅና ባላቸው ጆርናሎች ላይ በማሳተፍ ለተጠቃሚ ማህበረሰብ እንዲደረሱ መደረጉን ተናግረዋል። ሌሎች ከ66 በላይ የሚሆኑ ምርምሮች ደግሞ በጥናት ላይ እንደሚገኙ አስተባባሪው አስረድተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦችን እንደመነሻ በመጠቀም በአካባቢው ከሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ፕሮጄክቶች በመቅረጽ ስልጠናና ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ እንደ አቶ ተመስገን ገለፃ ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን  ችግር በቅርበት በመከታተል  የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ለማፋጠን የሚያስችሉ የምርምር ጣቢያዎችን በወረዳዎች ለመክፈት በዝግጅት ላይ ይገኛል። ከተጠቃሚ አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ ጀሚላ ሀሰን እንደተናገሩት “ዩኒቨርሲቲው ምርጥ ዘር እንዲጠቀሙ ባደረገላቸው ድጋፍ በእርሻ ስራ ጥሩ ውጤት አግኝቻለሁ” ብለዋል፡፡ የጡሎ  ወረዳ አርሶ አደር  እንዳሻው ሀይሌ በበኩላቸው “በተጨማሪ በመስመር የመዝራት ቴክኖሎጂን ጨምሮ ሌሎች የተሻሻሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ዘዴዎች ጋር እንድተዋወቅና እንድጠቀም ረድቶኛል'' ሲሉ ተናግረዋል። የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ በ2008 ዓ.ም ተከፍቶ ከሚያካሂደው የመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር የሚፈቱ ኘሮጀክቶችን በመቅረጽ እየሰራ መሆኑ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም