በአማራ ክልል በአዲሱ ዓመት 600 ሺህ ሕጻናት ትምህርት ቤት ይገባሉ

136
ባህር ዳር ነሐሴ 25 / 2011 በአማራ ክልል ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 600 ሺህ በአዲሱ ዓመት ትምህርት እንደሚጀምሩ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ሰሞኑን ለኢዜአ እንደገለጹት ዕድሜያቸው ሰባት ዓመት የሞላቸውን ህጻናት ወደ ትምህርት ለማስገባት እየተሰራ ነው። ወደ ትምህርት የሚገቡትን ሕፃናትን የመለየት ሥራውም በየአካባቢው በሚገኙ የወላጅ መምህራን ኅብረትና በትምህርት አመራር ከዚህ ወር ጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን  አስረድተዋል። የተማሪዎች ምዝገባ ከመስከረም 6 እስከ 11/2012 ድረስ እንደሚከናወንም ኃላፊው አመልክተዋል። በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ተሳተፎ የተገነቡ 113 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና 2ሺህ 770 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች መሰራታቸውን ተናግረዋል። እንዲሁም 481 የዳስ ትምህርት ቤቶችን ማሻሻልና ደረጃቸውን እንዲጠብቁ መደረጋቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ያረጁ የመማሪያ ክፍሎች እድሳትና የመማሪያ ወንበሮች ጥገና  መከናወኑን  አቶ ይልቃል አስታውቀዋል። በክልሉ በአንደኛ ደረጃ መማር ከሚገባቸው ተማሪዎች 20 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት መከታተል ያለመቻላቸው ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ። በምዕራብ ጎጃም ዞን የደንበጫ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ድንቃየሁ አለኽኝ በበኩላቸው በየቀበሌው ዕድሜያቸው ሰባት ዓመት ሞልቷቸው እየተለዩ ያሉ ህፃናትን ትምህርት ለማስጀመር ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ አንድም ህፃን የትምህርት ዕድል ሳያገኝ እንዳይቀር በመሰራት ነው ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ የትምህርት ጉዳዮች የስራ ሂደት መሪ አቶ ታያቸው ገብረስላሴ ናቸው። በዞኑ  ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን ትምህርት ቤት ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። በደሴ ከተማ የወላጅ መምህር ኅብረት ተጠሪ አቶ መሐመድ ሰኢድ በበኩላቸው ከከተማው አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ጋር በመቀናጀት ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመለየት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። በክልሉ በመጪው የትምህርት ዘመን 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም