ፍቼ ጫምባላላ ባህላዊ ስነስርዓቱን ጠብቆ ተጠናቋል- የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር

89
ሀዋሳ ሰኔ 7/2010 በአለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የሲዳማ ፍቼ ጫምባላላ በዓል ስነስርዓቱን ጠብቆ መጠናቀቁን የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደሴ ዳልኬ አስታወቁ፡፡ በዓሉን ተከትሎ በዋዜማውና በዕለቱ እንዲሁም በወልቂጤ ከተማ በተፈጠረው ግጭት  ለጠፋው የሰው ህይወትና ንብረት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት መግለጫ "የፍቼ ጫምባላላ በዓል የሲዳማ ብሔር ብቻ ሳይሆን የክልላችን፣ የሀገራችንና የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል" ሲሉ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ባህልና ቅርስ በየዓመቱ በባህሉ ባለቤትና ሌላም የሀገሪቱ ህዝቦች በጋራ ሆነው በደመቀ መልኩ የሚከበር በዓል በመሆኑ በዚህ ዓመትም በተመሳሳይ ስነስርዓቱን ጠብቆ መከበሩን ገልጸዋል፡፡ የዋዜማውን በዓል ለማክበር ወጣቱ በጊዜ እንደወጣ የተናገሩት አቶ ደሴ  በነበረው ከፍተኛ መጨናነቅ  መጠነኛ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል፡፡ የበዓሉ ባለቤት ወጣቱ ኃይል የበዓሉን እሴት የሚያጎድፍ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን መከላከልና መከታተል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በወቅቱ ያጋጠመውን ችግር ብሄር ተኮር አስመስሎ በማህበራዊ ሚዲያ ማራገቡ ተገቢ አለመሆኑንም ነው ያመለከቱት፡፡ በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ የነበረውን ስጋት  አመራሩ ከህግ አስከባሪዎች ጋር ተባብሮ በማረጋጋት  ችግሩን መቆጣጠር መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ  በሁለት እግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ግጭት በማምራቱ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱንም አቶ ደሴ አመልክተዋል፡፡ የአካባቢውን ህብረተሰብንና የጸጥታ አካላትን  ያሳተፈ ስራ በማከናወን ለማረጋጋት ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በግጭቱ ለጠፋው  የሰው ህይወትና ንብረት የተሰማቸውን ሃዘን በክልሉ ህዝብና መንግስት ስም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም