ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የስነ-ምግባር ኮሚቴ ውሳኔ በድጋሚ እንዲታይ ጠየቀ

118
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስነ-ምግባር ኮሚቴ ውሳኔ በድጋሚ ይታይልኝ ሲል ይግባኝ ጠየቀ። የፌዴሬሽኑ የስነ-ምግባር ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም በጅማ ስታዲየም ጅማ አባጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጉት የ25ኛ ሳምንት ጨዋታ በተፈጠረው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ምክንያት በሁለቱ ቡድኖች ላይ ቅጣት መጣሉ ይታወሳል። በውሳኔው የጅማ አባጅፋር ቡድን 150 ሺህ ብር እንዲቀጣ፥ እንዲሁም አንድ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ በፌዴሬሽኑ በተመዘገበ ሜዳ እንዲጫወት ተወስኖበታል፡፡ በተጨማሪም የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለፌዴሬሽኑ በሚያቀርበው የህክምና ማስረጃ መሰረት በክለቡ ደጋፊዎች ላይ ለደረሰው ጉዳት ጅማ አባጅፋር ካሳ እንዲከፍል ኮሚቴው ወስኗል። የስነ-ምግባር ኮሚቴው ፌዴራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ ለጅማ አባጅፋር የቅጣት ምት መስጠታቸውን ተከትሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሜዳ ገብተው ዳኛውን ለመደብደብ ሙከራ አደርገዋል በሚል ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የ50 ሺህ ብር ቅጣት አስተላልፏል፡፡ እንዲሁም በጨዋታው ወቅት ስድስት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች አምስት ቢጫ እና አንድ ቀይ ካርድ በመመልከታቸው የዲሲፕሊን ኮሚቴው ቡድኑ አምስት ሺህ ብር እንዲቀጣ ነው የወሰነው፡፡ ክለቦቹ የተወሰነባቸውን ቅጣት በ10 ቀናት ውስጥ ገቢ እንዲያደርጉ የታዘዙ ሲሆን፥ ይህንን ተፈጻሚ የማያደርጉ ከሆነ ከውድድር እንዲታገዱና ከፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ምንም ዓይነት ትብብር እንዳያገኙ መወሰኑን አሳውቆ ነበር። ይህን ተከትሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የስነ-ምግባር ኮሚቴ የወሰነው ውሳኔ" ኢ-ፍትሐዊ" ሲል ክለቡ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ በተላለፈው የቅጣት ውሳኔ ዙሪያ ይግባኝ መጠየቁን ገልጿል። በስነ-ምግባር ውሳኔው ተራ ቁጥር አንድ የተጠቀሰውን የሚያፈርስ፤ ለጸቡ መነሻም መድረሻም ባለሜዳው ቡድን መሆኑን እንደሚያረጋግጥ መገለጹን ጠቁሟል። "የተጠቀሰው እኛ ግብ ካስቆጠርን በኋላ በሁለቱም ደጋፊዎች መካከል ረብሻ ተነስቶ ድንጋይ ሲወራወሩ ነበር የሚለው በገሀድ የታየውን እውነታ በመለወጥ የባለሜዳውን ቡድን ጥፋት ለመሸፈን የተደረገ ጥረት ነው፤ በንፁህ ህሊና ስናስበው ግብ ያስቆጠረ ቡድን በውጤቱ ረክቶ ይደሰታል፣ ይጨፍራል፣ ይዘምራል እንጂ ለሥነ-ምግባር ጥሰት የሚያነሳሳው አንድም ምክንያት አይኖርም" ብሏል የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ። ኮሚሽነሩ የተሰጣቸውን ተግባርና ሀላፊነት በሚገባ እንዳይወጡ በጅማ አባ ጅፋር ክለብ ደጋፊዎች ማስፈራራት እንደደረሰባቸውና ሊደበድቧቸውም እንደነበር በጽሑፍ ገልፀው የዲሲፕሊን ኮሚቴው ግን ጉዳዩን አቅልሎ ለባለሜዳው ቡድን በ2009 ዓ.ም በወጣው የተሻሻለው የስነ-ምግባር መመሪያ አንቀጽ 66 መሠረት ተገቢውን ቅጣት ያልሰጠበት ምክንያት ግልጽ አይደለም ነው ያለው። የስነ-ምግባር ኮሚቴ ያቀረብነውን መረጃ ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ እንጂ በኛ በኩል በመቅረቡ ብቻ ገለልተኛ ስላልሆነ በሚል በግልጽ፣ በፎቶ እና በፊልም የተደገፉ ሀቆችን መካድ ወይም አለመቀበል ተገቢ አይደለም ብሏል። ክለቡ በጨዋታው ማግስት ለፌዴሬሽኑ ባስገባው ህጋዊ ደብዳቤ በቂ ሀይል ሳይኖር ጨዋታው መጀመር እንዳልነበረበት የገለጸ መሆኑንና የጥበቃ ተግባርም ያልተፈጸመው በባለሜዳው ቡድን በመሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከ2010 እስከ 2012 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊግ ወንዶች ክለቦች የውድድር ደንብ ምዕራፍ 3 አንቀጽ 1 ለ በሚያዘው መሠረት ተገቢው ዕርምጃ ሊወሰድበት ይገባ እንደነበርና የስነ-ምግባር ኮሚቴው ግን በቸልተኝነት እንዳለፈው ክለቡ ባቀረበው ይግባኝ ላይ ተጠቅሷል። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ለ44 ደቂቃ የተቋረጠ ጨዋታ መልሶ እንዲቀጥል የተደረገበት ሁኔታ አግባብነት የሌለው ስለሆነ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተሻሻለው የዲሲፕሊን መመሪያ አንቀጽ 72 ንዑስ አንቀጽ 4 መሠረት መፈጸም ሲገባው የጨዋታው ኮሚሽነር ከደንብና ከስልጣናቸው ውጪ ጨዋታውን ማስቀጠላቸው "ህገ-ወጥ" ነው ሲል የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ አስታውቋል። ተመልካቾች ከሜዳው መስመር በአንድና በሁለት ሜትር ርቀት ላይ ባሉበት ሁኔታ ጨዋታው እንዲቀጥል መወሰን ራሳቸውን ዳኞቹንና የሁለቱንም ቡድን ተጫዋቾች ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ ደካማ ውሳኔ ነበር፡፡ በዚህ የጨዋታው አመራሮቹ ስህተት የተነሣ የተሰጠው አድሏዊ የፍጹም ቅጣት ምት ውሳኔ ተጨምሮበት እነዚህን አስቀድሞ ሜዳ ውስጥ እንዲገኙ የተፈቀደላቸውን ተመልካቾች ተጠያቂ ማድረግ አግባብነት የለውም ሲል ክለቡ ለፌዴሬሽኑ ያስገባው ይግባኝ ያስረዳል። በአጠቃላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የተጣለው የ50 ሺህ ብር ቅጣት እንዲነሳና የባለሜዳው ቡድን ላይ የተጣለው ቅጣት የበፊት ጥፋቶችን ያላገናዘበና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስነ-ምግባር ደንብ እና የ2010 ዓ.ም የውድድር ደንብን ያልተከተለ ስለሆነ ህጉ በአግባቡ እንዲተገበር እንጠይቃለን ሲል የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ገልጿል። ጅማ አባ ጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጉት ጨዋታ በአንድ ለአንድ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም