በኢትዮጵያ ድርቅን ለመከላከል የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂን መጠቀም ያስፈልጋል

165
ነሀሴ 23/2011 በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተከሰተ ጉዳት የሚያደርሰውን ድርቅ ለመከላከል የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
ተመድ ዓለም ላይ ካሉት 23 ሳተላይቶች ጋር የኢትዮጵያን ሳተላይት እንደሚያስተሳስር አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በህዋ መረጃ ላይ የተመሰረተ የአደጋ መከላከልና አፋጣኝ ምላሽ ክፍል ጋር በመተባበር ድርቅን እንዴት መከላከል እንደሚገባና በቅድመ ትንበያ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ እንዳሉት፤ ስፔስ ሳይንስ መረጃን በመጠቀም ድርቅ ለመከላልና መረጃ የሚያግዝ መረጃ የመሰብሰብ ልምድ አልነበረም።
ይህንን ሁኔታ በመቀየር ድርቅን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል መረጃ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
''የኢትዮጵያ ሳተላይት በዚህ ዓመት ወደ ህዋ ይመጥቃል፣ ትልቅ የሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ እየተገነባ ይገኛል፤ ይህም የብዙ ሳተላይት መረጃዎችን ለመሰብሰብ ያግዛል'' ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኢንስቲትዩቱ ከበርካታ ሳተላይት ተቋማት ጋር ግንኙነት ስላለው በቀላሉ የሚፈለገውን መረጃ ለማግኘት እንደሚያስችል ተናግረዋል። በዓለም ላይ ግብርናን ለማዘመን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው የሳተላይት መረጃ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን ግብርና ለማዘመን የኢንስቲትዩቱ ዋና ግብ መሆኑን ጠቁመዋል። በአገሪቱ ከዚህ ቀደም 10 አመታትን ያህል እየጠበቀ የሚከሰተው ድርቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁሉም ክልሎች በየሶስት ዓመቱ እየተከሰተ በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለጉዳት እየዳረገ እንደሆነ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአየር ንብረት ምርምር ባለሙያ ዶክተር ደግፌ ጥበበ ድርቅ በግብርና ምርቶች፣ በእንስሳትና በሰዎች ላይ በየጊዜ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከልክና አስቀድሞ ለማወቅ የህዋ መረጃ እንደሚያግዝ ተናግረዋል። የተለያዩ የሳተላይት መረጃዎችን በማሰባሰብ፣ በመተንተንና ድርቅን የመከላከል ብሎም ሊደርስ የሚችለውን ድርቅ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል አስረድተዋል። ''መረጃዎችን ከምድር ላይ በሳተላይት አማካኝነት በመሰብሰብ እና ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ቀድሞ በማወቅ የሚደርሰውን ጉዳት ቀድመው ለመከላከል ያስችላል'' ብለዋል። ''መረጃውን የሚጠቀሙ አካላት አስቀድመው ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ያስችላቸዋል'' ያሉት ዶክተር ደግፌ፤ የተለያየ ስትራቴጂዎችን ለመቅረጽ እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል። የተመድ በህዋ መረጃ ላይ የተመሰረተ የአደጋ መከላከልና አፋጣኝ ምላሽ ክፍል ቁጥጥር ባለሙያ ዶክተር ጁዋን ካርሎስ በበኩላቸው ሳተላይትን በመጠቀም ድርቅን ለመከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የቴክኒክ ድጋፍ ለኢትዮጵያ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ''መረጃውን በመጠቀም በጊዜው የሚደርሰውን ድርቅ ለመግታት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል'' ብለዋል። ''ዓለም ላይ ካሉት 23 ሳተላይቶች ጋር ተመድ የኢትዮጵያን ሳተላይት እንደሚያስተሳስርና በዚህም በቀላሉ የመረጃ ልውውጥ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል'' ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም