በፀደቀው የምርጫ አዋጅ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተለያየ አቋም ይዘዋል

53
ነሀሴ 23/2011ባለፈው ቅዳሜ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባፀደቀው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ላይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። ምክር ቤቱ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው ሶስተኛው አስቸኳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅን በሙሉ ድምፅ ነው ያፀደቀው። በአዋጁ መሰረት አንድ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ የ10 ሺህ አባላትን ድጋፍ ማግኘት ሲኖርበት የክልል ፓርቲዎች ደግሞ የአራት ሺህ አባላት ድጋፍ ይጠበቅባቸዋል። ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በረቂቅ አዋጁ ላይ እንዲወያዩና ግብዓት እንዲጨምሩ ዕድል እንደተሰጣቸውም አውስተዋል። እነርሱም አዋጁ ላይ መስተካከል አለባቸው ያሏቸውን ሀሳቦች ከምርጫ ቦርድ ጋር ባካሄዱት ውይይት መግለጻቸውን አስረድተዋል። ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያነሷቸው ሀሳቦች ሳይካተቱ አዋጁ እንዲፀድቅ መደረጉ አግባብነት አንደሌለው ነው የገለጹት። ይህ አሰራር ቀደም ሲል ገዥው ፓርቲ ሲያደርግ እንደነበረው ሆን ተብሎ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማዳከምና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማጥበብ የተደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል። የከምባታ ሕዝቦች ኮንግረስ ሊቀመንበር ኤርጫፎ ኤርዲሎ  በጥያቄቸችን  ላይ ያተኮረ  ሳይሆን ነና ምርጫ ቦርድም ከኛ ጋር ከተስማማው ሀሳብ ለየት ያለ ነው በመሆኑ ጨርሶውኑ የፖለቲካ   ምህዳር እንዳይኖር ያደርገዋል ብለዋል፡፡ የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ፋይሰል አብዱልአዚዝ ''ለወደፊቱ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚደረግበትን መንገድ መፈለግ ነው እንጂ ሌላውን ለመጣል መስፈርቱን የሚያወጣ አካል ምርጫ ቦርድ መሆን የለበትም፤ ምርጫ ቦርድ ህግ አስፈጻሚ እንጂ ህግ አውጪ አይደለም።" ሲሉም ተችተዋል፡፡ የኢዜማ ፓርቲ አባል አቶ ተሻለ ሰብሮ ግን የተለየ ሀሳብ አላቸው።እርሳቸው እንደሚሉት አዋጁ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳተፈና ቀደም ሲል በምርጫ አዋጁ ላይ ያጋጥሙ የነበሩ ማነቆዎችን የፈታ ነው። ''ፖለቲካ ፓርቲዎች በህግ የተሰጠን አስተያየት እንድንሰጥ ምርጫና ምርጫን በተመለከተ ነው እንጂ ህግ አውጪ ባለቤቶች አይደለንም'' ብለዋል። በረቂቅ አዋጁ ላይ ፓርቲዎቹ መሻሻል አለባቸው ያሏቸውን ነጥቦች ማንሳታቸውንና የሚሻሻሉ ጉዳዮችን አስተካክሎ የማፅደቁ ሚና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑንም አብራርተዋል። አዋጁ በዋናነት የምርጫ ሥርዓት፣ የምርጫ አፈፃጸም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረትና አስተዳደር፣ የምርጫ ስነ-ምግባር፣ በምርጫ ሂደት የሚነሱ ክርክሮች የሚዳኙበትና የሚፈቱበትን የአሰራር ስርዓት የያዘ ነው ተብሏል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀናጁበትንና እንደ አዲስ የሚዋሀዱበትን ዝርዝርም አካቷል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶልያና ሽመልስ ለኢዜአ በስልክ እንደተናገሩት በምርጫ ህጉ ረቂቅ አዋጅ ላይ ለስምንት ወራት በተካሄደው ጥናት የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትም ሲሳተፉ ቆይተዋል። የሕግ አርቃቂ ኮሚቴው ከአገርና ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታና ተሞክሮ በመነሳት ረቂቅ አዋጁ እንዲዳብር የተደረገ መሆኑንም አውስተዋል። አዋጁ ከመጽደቁ በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያነሷቸው የማሻሻያ ሃሳቦችና ቅሬታዎች ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መቅረባቸውንም  አስረድተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም