የኦሮሚያ የከተሞች ቀን ፎረም በጅማ ሊዘጋጅ ነው

114
አዲስ አበባ ሰኔ 7/2010 ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሳለፍ የከተሞች ልማትና እድገት መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ። በኦሮሚያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰኔ 18 እስከ 22 በጅማ ከተማ የሚካሄደውን የኦሮሚያ የከተሞች ቀን ፎረምን አስመልክቶ ዛሬ በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። የኦሮሚያ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ግርማ አመንቴ በመግለጫው እንደተናገሩት፤ "በአገራችን ካሉት ከተሞች ግማሽ ያህል  የሚገኙት በክልሉ ነው"። በክልል ደረጃ ይህ ፎረም መካሄዱ ከተሞቻችን የኢንቨስትመንት ማዕከላት በመሆናቸው ባለሀብቶች ያሉትን የስራ አማራጮች በአንድ ቦታ እንዲመለከቱ ያስችላቸዋል ብለዋል። አገሪቷ ለጀመረችው የኢንዱስትሪ መር ጉዞ እውን መሆን 15 በመቶ የሆነው የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ከተሞችን በማስፋፋት እና በማልማት ቁጥሩን ከፍ ማድረግ ይገባል ነው የተባለው። "የከተሞቻችን እድገትና ደረጃቸው የተመጣጠነ አይደለም" ያሉት ኃላፊው  አንዱ ከሌላኛው ልምድ እንዲወስድም ይህ ፎረም የጎላ  ሚና ይኖረዋል ብለዋል። በሌላ በኩል በፎረሙ በክልሉ ባሉት ከተሞች የሚስተዋሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የአገልግሎት አሰጣጥ እጥረት  በተመለከተ ከምርምር ተቋማትና ከዩኒቨርሲቲዎች ከተውጣጡ ምሁራን ጋር የፓናል ውይይት ተደርጎ የመፍትሔ ሀሳብ እንደሚቀመጥ ተገልጿል። መልካም ተሞክሮ ያላቸው ከተሞች በምሳሌነት በማቅረብም በፓናሉ ላይ እንዴት የመልካም አስተዳደር ስርዓቶች ማስፈንና መጠቀም እንደቻሉ ልምዶቻቸውን የሚያካፍሉበት ሂደት እንዳለም ተጠቁሟል። በኦሮሚያ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ይህ የከተሞች ቀን ፎረም በክልሉ የሚገኙት ሁሉንም ከተሞች ለማሳተፍ እድል የሰጠ ሲሆን እስካሁን ከ130 በላይ ከተሞች ለመሳተፍ እንደተመዘገቡ ተገልጿል። በክልሉ ያሉት ሁሉም ከተሞች በፎረሙ እንዲሳተፉ መደረጋቸው ተፎካካሪ እንዲሆኑና ባህልና እሴቶቻቸውን በጋራ እንዲያሳድጉ ያደርጋቸዋልም ተብሏል። ፎረሙ  በሚቆይባቸው 5 ቀናትም ኤግዚቢሽንና ባዛር የሚካሄድ ሲሆን ከተሞቹ እርስ በእርሳቸው በደንብ እዲተዋወቁ እድል የሚፈጥር መሆኑም ተገልጿል። ካሉት የኦሮሚያ ከተሞች የጅማ ከተማ በአዘጋጅነት መመረጧም ጥንታዊና ታሪካዊ የሆነች ከተማ በመሆኗ ነው ተብሏል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም