ኢትዮጵያ የኤም አይ ቲ አካታች የኢኖቬሽን ውድድር ጉባኤን በመጭው መስከረም ታስተናግዳለች

60
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 22/ 2011 የአንድ አፍሪካ ብሮድ ባንድ ኔትዎርክ አካል በሆነው ሊክዊድ ቴሌኮም አዘጋጅነት የሚከናወነው የአፍሪካ ኤም አይ ቲ አካታች የኢኖቬሽን ውድድርና ጉባዔ የፊታችን መስከረም ወር በአዲስ አበባ ይካሄዳል። በአፍሪካ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ አተኩሮ የሚሰራው አይ ኤ የተባለ ድረ ገፅ ይፋ እንዳደረገው ውድድሩና ጉባዔው መስከረም 28 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ ከ35 የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ 400 ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። ዝግጅቱን በማስተባበር የኢትዮጵያ መንግስት በአጋርነት እየሰራ ሲሆን በአገሪቷ ያሉ ወጣቶችን በመደገፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠር ይጠቀምበታል ተብሏል። የመንግስት አጋርነት የፓን አፍሪካን ትስስር በማጎልበት በአገሮቹ መካካል ያለውን መልካም ተሞክሮ ለመጋራት እንደሚያስችልም የኢኖቬሽንና ቴክኖለጂ ሚኒስቴር ዴኤታ ሲሳይ ሞላ ተናግረዋል። ዘርፉን የሚያበረታታ ፖሊሲ ማውጣት፣ የመሰረተ ልማት ማስፋትና የቴክኖለጂ ብቃትን ማሳደግ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው “ከኤም አይ ቲ ጋር በመተባበር ለአይሲቲ ተቋማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንሰራለን" ብለዋል። በዚህም በትክክለኛው መንገድ የፈጠራ ብቃትን ማሳደግና አካታችትን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል። ሊክዊድ ቴሌኮምም አፍሪካን በዘርፉ ወደ ፊት ለመምጣት የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፍ አስታውቋል። የሊኪዊድ ቴሌኮም የኢኖቬሽንና ቴክኖለጂ ክፍል ኃላፊ ቤን ሮበርት “ወደ አራተኛው ትውልድ የኢንዱስትሪ አብዮት እየገባን ያለንበት ወቅት በመሆኑ አፍሪካን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋገሩ ዘመናዊ ቴክኖለጂዎችንና ፈጠራዎችን ለማሳየት ከዚህ የተሻለ ጊዜ አለ ብለን አናምንም" ብለዋል። በአህጉሪቱ የሚገኙ ብሩህ አእምሮ ያላቸው የቴክኖለጂ ፈጣሪዎች የመጨረሻ ውድድርን በመደገፋቸው መደሰታቸውን ገልጸው በቀጣይም ተወዳዳሪዎችን እናበረታታለን ብለዋል። ከወድድሩ ጎን ለጎን የሚከናወነው ጉባኤ በመላው አፍሪካ የሚገኙ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ቴክኖለጂን በመጠቀም የኢኮኖሚ እድሎችን የሚፈጥሩበትን አግባብ ያሳያል። ጉባኤው በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ የስራ ፈጠራ ኮሚሽንና በኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖለጂ ሚኒስቴር ትብብር የሚዘጋጅ ነው። ለመጨረሻው ውድድር ከተመረጡት 12 አፍሪካውያን መካከል ችግር ፈቺ የሆነውን ፈጠራቸውን መሰረት በማድረግ አሸናፊው ይለያል። በአራት ምድብ የተከፈለው ውድድር አራት አሸናፊዎችን በመለየት ህዳር 21 ቀን 2019 አሜሪካ ማሳቹቴሱትስ በሚደረግ ስነ ስርአት ይከናወናል። በውድድሩ የመጨረሻው አሸናፊ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ተሸላሚ እንደሚሆንም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም