መገናኛ ብዙሃን ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡብ ኮሪያና ጃፓን ጉብኝት ምንአሉ

98
በኢዜአ ሞኒተሪንግ ለኮሪያ ባህረ ሰላጤ ሰላም በጋራ ለመስራት የኢትዮዽያና የደቡብ ኮሪያ መሪዎች ቃል መግባታቸውን በመዘገብ መረጃውን ያሰራጨው አሪራንግ ድረ ገፅ የኢትዮዽያው ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የአሁኑ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ወደ ሃላፊነት ከመጡ በኋላ ኮሪያን የጎበኙ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ እንደሆኑም አንስቷል። ኢትዮዽያና ደቡብ ኮሪያ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ድረ ገፁ አክሎ እኤአ በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ በተካሄደው የሁለቱ ኮሪያዎች ጦርነት ወቅት ኢትዮዽያ ደቡብ ኮሪያን በመወገን የእግረኛ ጦር በማሰማራትም ከአፍሪካ ብቸኛዋ ሃገር እንደነበረች አስታውሷል። ሁለቱ ሃገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ መስማማታቸውን የዘገበው የደቡብ ኮሪያው ዜና ምንጭ ዮንሃፕ ፕሬዚዳንት ሙንጄ እና ጠ/ሚ አብይ አህመድ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በልማት መስክ፣ በደን ልማት እና በአካባቢ ጥበቃ በትብብር ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸውን ፅፏል። ደቡብ ኮሪያ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ለሚገነባው የምርምር ማዕከል የሚውል 86 ሚሊዮን ዶላር በብድር መልክ መስጠቷንም ዩንሃፕ አክሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የኮሪያ ቆይታቸውን በማጠናቀቅ ወደ ጃፓን ማቅናታቸውን የዘገበው ደግሞ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በድረ ገፅ ዘገባው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጃፓን ቆይታቸው በጃፓን አፍሪካ ልማት ፎረም(የቲካድ) ስብሰባ ላይ እንደሚሳተፉ ፋና ዘግቦ የጃፓኑ አቻቸው ሺንዞ አቤ ባቀረቡላቸው ግብዣ መሰረት የልማት ፎረሙ ስብሰባ ላይ እንደተገኙም አስነብቧል። ኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችላቸውን የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚቴ ለማዋቀር መስማማታቸውን የዘገበው ኮሪያን ሄራልድ የሃገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ያጠናክራል የተባለው ኮሚቴም በከፍተኛ ዲፕሎማቶቻቸው እንዲመራ ተግባቦት ላይ መድረሳቸውን ጠቁሟል። የሁለቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ኮሪያን ሄራልድ በመረጃው አካቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በጃፓን የቲካድ ስብሰባ ተሳትፎ ጎን ለጎን ከጃፓን ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩ የዘገበው ኢዜአ የአፍሪካ ህብረት ፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት(ዩኤንዲፒ) እና የአለም ባንክ የቲካድ ጉባኤ ተባባሪ አዘጋጆች መሆናቸውን ጠቁሟል። የመጀመሪያው የጃፓን አፍሪካ ልማት ጉባኤ(ቲካድ) እኤአ በ1993 መካሄድ መጀመሩን ያስታወሰው ኢዜአ “በህዝብ ፣ ቴክኖሎጂ ፈጠራ የአፍሪካን ልማት እናፋጥናለን” በሚል መሪ ቃል ጉባኤው ከነሃሴ 22 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ ለሶስት ቀናት እንደሚካሄድ አንስቷል። የኮሪያው ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (KBS) በበኩሉ የሁለቱ ሃገራት መሪዎች በተለያዩ ዘርፎች የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ዘግቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ባለፉት ስምንት አመታት ውስጥ ኮሪያን በመጎብኘት የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ መሆናቸውንም ኬቢሲ በዘገባው አስፍሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም