በጮቢ ወረዳ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ደብቆ የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

95
አምቦ ኢዜአ ነሐሴ 22 ቀን 2011 ዓም - በምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ወረዳ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ደብቆ የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ። የወረዳው ፖሊስ ፅህፈት ቤት የወንጀል መከላከል ኃላፊ ሳጅን ወርቅነህ ዲነግዴ ለኢዜአ እንደገለፁት ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ዛሬ ጧት አራት ሰዓት አካባቢ ነው ። ግለሰቡ በወረዳው ቆርጬ ጨቢ ቀበሌ በሚገኝ በአንድ በእድሜ የገፉ አዛውንት መኖሪያ ቤት ውስጥ ሶስት ቦምቦች፣ ሁለት ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎችና 198 ጥይቶች ከስድስት የጥይት መያዣ ካዝናዎች ጋር ደብቆ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል ። ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ግለሰቡ መያዙን የገለፁት  ሳጅን ወርቅነህ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ገለፀዋል ። ህብረተሰቡ አጠራጣሪ የሆኑ ድርጊቶች ሲከሰቱ በአፋጣኝ ለፖሊስ በማሳወቅ ወንጀልን ለመከላከል እያሳየ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ሳጅን ወርቅነህ  አስገንዝበዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም