የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባላት አገራዊ ለውጡን ለማራመድ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል- የመንግሥት ባለሥልጣን

56
ሐዋሳ ነሐሴ 21 /2011 የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባላት አገራዊ ለውጡን ለማራመድ እንዲንቀሳቀሱ አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ አሳሰቡ። የክልሉ የምክር ቤት አባላት በወቅታዊ አገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ የምክክር መድረክ ዛሬ በሐዋሳ ጀምረዋል። በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ማዕከል ምክትል ዋና አስተባባሪ አቶ መለሰ ዓለሙ መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት አባላቱ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ስኬታማነት መሥራት  አለባቸው። ለዚህም አባላቱ ለክልሉና ለሕዝቡ የሚበጁ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ክልላዊና አገራዊ ሁኔታዎችን መገንዘብ ያሻችኋል ብለዋል። የክልሉ መንግሥት በሚያከናውናቸው ተግባራት በአሳታፊነት በማስተባበርና በመምራት ሕዝቡንና ክልሉን ወደተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚያስፈልግ አቶ መለሰ አስገንዝበዋል። ምክር ቤቱ በቀጣይ በሚያደርጋቸው ጉባዔዎች የሕዝቦችን ጥቅም የሚያስከብሩና ክልሉን ወደተሻለ ደረጃ የሚያደርሱ ውሳኔዎችን ማሳለፍ እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል። አባላት ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚቆየው መድረክ በአገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ ጉዳዮችና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ባስጠናው የክልል መዋቅር ጥናት ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም