አገራዊ ለውጡ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እስኪያገኝ ጊዜ ይፈልጋል - የታሪክ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ

68
ነሀሴ 21/2011 አገራዊ ለውጡ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እስኪያገኝ ጊዜ እንደሚፈልግ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ባህሩ ዘውዴ ገለጹ። ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው ''የለውጥ ሂደቱ ያጋጠሙት ችግሮች የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ መገምገም አለባቸው'' ብለዋል። የኢትዮጵያ አገራዊ ለውጥ ሂደት ወቅታዊ ሁኔታ፣ እድል፣ ተግዳሮትና ስጋቶች' በሚል ሰሞኑን በተደረገው ስብሰባ ተሳታፊ የነበሩት የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፈሰር ባህሩ ዘውዴና ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው በተለይ ለኢዜአ አስተያይት ሰጥተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤምሬትስ ፕሮፈሰሩ ባህሩ ዘውዴ፤ ኢትዮጵያ በስርዓተ መንግስት ታሪኳ ለውጥ ማካሄድ አዲሷ እንዳልሆነ ይናገራሉ። በዘመናዊ ታሪኳ እንኳን ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ለማዋሃድ መነሳታቸውን፣ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ደግሞ ተቋማትን በማቋቋም ዘመናዊ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮክራሲ ምስረታ ማስጀመራቸውን፣ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በርካታ መንግስታዊ ስርዓት ማሻሻያ ማካሄዳቸውን ያስታውሳሉ። ዳሩ ግን የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ለውጥ ሳይሳካ የለውጥ አራማጁ ህይወት መቀጠፉን እንዲሁም በመጨረሻ ንጉሳዊ ስርዓት በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን በርካታ ለውጥ ቢደረግም የለውጥ ሂደቱ ሳይሰምር መቅረቱን ገልጸዋል። በተለይም ሁለት ህገ መንግስቶች ቢወጡም ሁለቱም ድክመት የነበራቸው፣ የንጉሱን ሃይል ለማጠናከር፣ መሳፍንቱን ለመቆጣጠር እንጂ የህዝብን ጥቅም ማዕከል ያላደረጉ፣ መብቶችን ያላስከበሩ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህም በውርስ ንጉሳዊ ስርዓት የተመሰረተው ለውጥ የንጉሰ ነገስቱ ስልጣን በህገ መንግስት ባለመገደቡ፣ አብዮቱን ያስከተለውና አገሪቱን ወደሌላ ቀውስ የከተተው ለውጥ እንዲከሰት ማድረጉን አውስተዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ የመጣ መሆኑን የሚገልጹት ፕሮፌሰር ባህሩ፤ ለውጡ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እስኪያገኝ ድረስ ጊዜ እንደሚፈልግ አስገንዝበዋል። ለውጡን ስኬታማ ለማድረግና የአገር ህልውናን ለማስቀጠል የብሄር ማንነትና ኢትዮጵያዊነት ሳይቃረኑ ተሳስረው እንዲሄዱ ማስቻል ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል። ማህበራዊ እሴቶችንና ባህላዊ ሃብቶችን የፖለቲካ ስርዓት ግብዓት ሆነው እንዲጠቅሙ ማድረግ ተገቢነት እንዳለው ፕሮፌሰር ባህሩ አንስተዋል። ሌላው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው የአሁኑ የኢትዮጵያ አገራዊ ለውጥ ሲጀመር በህዝብ ዘንድ ተስፋ የተጣለበትና ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘ እንደነበር አንስተዋል። ይሁንና አንድ ዓመት ከስድስት ወር ያስቆጠረው አገራዊ ለውጥ ህዝቡ በሚፈለገው ዘለቄታዊ መፍትሄ ባለመራመዱ ህዝቡን ለጥርጣሬ እየዳረገ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። መዋቅራዊ ዴሞክራሲ የሚጠበቅ ቢሆንም የለውጡ ሃይል ስለለውጡ ችላ እያለ መሆኑን በማንሳት፣ ገዥው ፓርቲ ሽኩቻ ውስጥ መግባቱን ገልጸዋል። ''ለውጡ ካሉት በጎ ጎኖች ይልቅ ችግሮቹ ሲመዘኑ ይጎላሉ'' ያሉት አቶ ልደቱ፤ የለውጥ ሂደቱ ያጋጠሙትን ችግሮች የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀትና መገመግም ተገቢ እንደሆነ አንስተዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም