ውሳኔው ሰላምን በማስፋን ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ያግዛል—ምሁራን

917

መቀሌ ሰኔ 7/2010 የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በኢትዮ ኤርትራ ድንበር ጉዳይ በቅርቡ ያሳለፈው ውሳኔ ዘላቂ ሰላም በማስፈን ልማትንና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እንደሚያግዝ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለጹ፡፡

በዩነቨርስቲው  በተለያዩ የምርምር ስራዎች ላይ የተሳተፉት ፕሮፌስር  ምትኩ ኃይሌ  ለኢዜአ እንዳሉት የሁለቱም ሀገራት ድንበር አካባቢ ላለፉት ሀያ ዓመታት በነበረው የጦርነት ስጋት  ከልማትና ኢንቨስትመንት ስራዎች ርቆ ቆይቷል፡፡

” የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት  በአካባቢው የሚገኙ የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች የልማት ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል” ብለዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች አብረው የኖሩና የተዛመዱ በመሆናቸው የድንበር የይገባኛል ጥያቄም እነሱን በማማከር ሊፈታ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ያስተላለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ኤርትራዊያን ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ፕሮፌሰር ምትኩ ተናግረዋል፡፡

“ላለፉት ሀያ አመታት ተዘግቶ የቆየውን ኢንቨስትመንትና የተቀላጠፈ ልማት እንዲኖር ይረዳል ” ያሉት ምሁሩ ውሳኔው ሁለቱም መንግስታት በአሸናፊነት የሚወጡበት እንደሚሆንም ያላቸው እምነት ገልጸዋል።

በዩኒቨርስቲው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የማነ ዘርአይ በበኩላቸው ሁለቱም ሀገራት በሚያዋስናቸው 900 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው አካባቢ ላለፉት ሀያ ዓመታት ትርጉም ያለው የኢንቨስትመንት ስራ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡

ለዚህም ምክንያቱ  አካባቢው የጦርነት ቀጠና ሆኖ በመቆየቱ ነው።

“ኢንቨስትመንትና የስራ ፈጠራ ከሌለ በዋናነት  ተጎጂው የሁለቱም ተጎራባች ህዝቦች ናቸው”ብለዋል፡፡

ሁለቱም መንግስታት ስምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ  ለዘላቂ ልማታቸው  ህዝቦቻቸውን የማቀራረብ ስራ ማከናወን እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በተለይም በሺዎች  የሚቆጠሩ የኤርትራ ወጣቶች  ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚያደርጉት ስደት ሊታደጋቸው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በነበረው ችግር ከልማት ስራዎች ርቆ የቆየው የሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ  ያሳለፈው ውሳኔ ዘላቂ ሰላም በማስፈን ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እንደሚያግዝ ነው ምሁራን የተናገሩት፡፡