በድሬዳዋ የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል ፕሮጀክት እየተከናወነ ነው

3252

ድሬዳዋ ሰኔ 7/2010 በድሬዳዋ አስተዳደር  የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ በ80 ሚሊዮን ብር የመከላከያ ፕሮጀክቶች እያከናወነ መሆኑን የከተማዋ  መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።

ባለፉት ስድስት ዓመታት በገጠር የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ጎርፍ የሚያስከትለውን አደጋ ከመከላከል በተጨማሪ የጎርፍ ውሃ  ለልማት ማዋል መቻሉን  የአስተዳደሩ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ  አቶ ሕዝቅያስ ታፈሰ እንደተናገሩት ክረምትን ተከትሎ ሊደርስ የሚችልን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል በገጠርና በከተማ የተለያዩ የመከላከያ ፕሮጀክቶች  እየተከናወኑ ነው።

በ1998 ዓ.ም. በድሬዳዋ የደረሰውን ጎርፍ ተከትሎ በድሬደዋ ከተማና ገጠር አካባቢ የጎርፍ መከላከል ስራ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰዋል።

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ እስከ አለፈው ዓመት ድረስ በደቻቱና በቡቲጂ ወንዞችና በሌሎች አካባቢዎች ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የጎርፍ መከላከያ ግንብ በመስራት ሊደርስ የሚችለውን የጎርፍ አደጋ መቀነስ ተችሏል፡፡

ዘንድሮም አምና በጎርፍ የፈረሰን 1 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የመከላከያ ግንብ የመጠገንና   አንድ ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር አዲስ የመገንባት ሥራ በመልካና በጎሮ አካባቢዎች እየተገነባ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከመከላከያ ግድቡ በተጨማሪ የጎርፍ መውረጃዎችን በማስተካከልና ውሃው ያለጥፋት እንዲጓዝ የሚያስችሉ የጠረጋ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

የገጠር ወንዞች አደጋ እንዳያስከትሉ  የሚያግዙ 40 ኪሎ  ሜትር የጋብዩን ሽቦ በመጠቀም  የድንጋይ ክትርና የጎርፍ መከላከል ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ግን በመንደር ውስጥ የሚገኙ የውሃ መውረጃ ቦዮችና ዲቾች በአፈር፣ በፕላስቲክ ጠርሙስና በግንባታ ተረፈ ምርቶች እየተሞሉ ለጎርፍ አደጋ መንስኤ እየሆኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በአቅራቢያው የሚገኙ ዲቾችን በባለቤትነት በመጠበቅና በማጽዳት ከጎርፍ ስጋት ራሱን የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአስተዳደሩ ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሃብት ልማት አብይ የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ኤሊያስ አልይ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ጎርፍ ከከተማ በተጨማሪ የገጠሩ ህብረተሰብ ማሳ በማውደምና እንስሳቱ በጎርፍ እየወሰደ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል፡፡

”ለጎርፍ አደጋ ዋና መንስኤ የገጠሩ የተራቆተው አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው ባለፉት 6 ዓመታት በ48 ሺ 4 መቶ የተራቆተ አካባቢን የአፈርና የውሃ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ በመከናወኑ ችግሩ እየቀነሰ መጥቷል” ብለዋል፡፡

በተጨማሪ ውሃውን ለመስኖ ልማት በማዋል ከ2ሺህ 540 በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አቶ ኢሊያስ ገልጸው ቀደም ሲል በጎርፍ ይታጠብ የነበረውን ለም አፈር መጠበቅ መቻሉን አስረድተዋል።

እንዲሁም ውሃውን ወደ ማሳ  በማስረግ እርጥበትን ማቆየትና የከርሰምድር ውሃ መጠን ከፍ ማለቱን ገልፀዋል፡፡

በድሬደዋ የአዲስ ከተማ አካባቢ ነዋሪ  ወይዘሮ እጅጋየሁ አበበ በሰጡት አስተያየት ከ12 ዓመታት በፊት የደረሰውን የጎርፍ አደጋ ተከትሎ በደቻቱ ወንዝ የተሰሩት መከላከያ ግንቦች ለህብረተሰቡ እፎይታን ሰጥተዋል፡፡

በወንዙ ውስጥ ያለውን አሸዋ የሚዝቁና ለግንቡ መሠረት መፍረስ መንስኤ የሚሆኑትን አካላት ህብረተሰቡ እየተከላከላቸው እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

”የመከላከያ ግንብ መሰራት አንዱ የጎርፍ መከላከያ መንገድ ቢሆንም አካባቢውን ለተመሳሳይ ችግር የሚዳርገው የፍሳሽ ማስወገጃ  ቦዮች አለመኖርና ያሉትም በቆሻሻ በመደፈናቸው ነው” ያሉት ደግሞ በጎሮ አካባቢ የሚኖሩት አቶ አሊ ሰመተር ናቸው።

በተመሣሣይ ዜና በ38ቱ የድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች የተሰራው የተፋሰስ ልማት ጎርፍ በእርሻና በእንስሳት ሃብት ላይ የሚያስከትለው ችግር ከማቃለል ባለፈ ውሃውን ለልማት ማዋል መቻሉን የአስተዳደሩ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በግብርና ጽህፈት ቤት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ባለሙያ አቶ አያሌው አርአያ እንደገለፁት የተቀናጀው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ  በጎርፍ ይደርስ የነበረን የእርሻ መቆረጥ፣ የመኖ መጥፋት፣ ከአካባቢ መፈናቀልና የምርት መቀነስ አስቀርቷል።

በተጨማሪ ከምስራቅ ተጎራባች አካባቢዎች ወደ ድሬዳዋ ከተማ በመፍሰስ አደጋ ያደርስ የነበረን ጎርፍ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የለገኦዳ ጉኑንፈታ ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር ሙሜ አደም ”በተፋሰስ ልማቱ የተሰሩ የአፈርና የድንጋይ ክትሮችና መሰል ልማቶች በክረምት ወቅት ይደርስ የነበረን የጎርፍ አደጋ  መከላከል አስችሏል” ብለዋል፡፡

”ከ5 ዓመት በፊት በማሳዬ ላይ የዘራሁት በቆሎና ማሽላ ሙሉ በሙሉ በጎርፍ ወድሞብኝ ለችግር ተዳርጌ ነበር፤ ከተፋሰስ ልማቱ ወዲህ ግን ይህን መሰል ችግር አጋጥሞኝ አያውቅም”  ሲሉ ገልፀዋል፡፡