በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የግብርና ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

73
ፍቼ (ኢዜአ) ነሐሴ 20 ቀን 2011---በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በዘንድሮ የመኸር እርሻ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ምርታማነትን በአጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በመኸር እርሻው ከ176 ሺህ የሚበልጡ የዞኑ አርሶ አደሮች ማሳቸውን በተለያዩ ሰበሎች አልምተው ምርታቸውን በእጥፍ ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑም ተመልክቷል ፡፡ የጽህፈት ቤቱ የአዝርዕትና ኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ ደረጄ ኤጀታ እንደገለጹት ከሰኔ ወር መጀመሪያ ጀምሮ በዞኑ13 ወረዳዎች 623 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ ነው። መሬቱ ጤፍ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ምስር፣ ባቄላና አተር ባሉ ሰብሎች መሸፈኑን ገልጸው፣ ቀሪ 71 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ጤፍን ጨምሮ ሌሎች ዘግይተው በሚዘሩ ሰብሎች ለመሸፈን የእርሻ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል። “ለስራው ውጤታማነት 154ሺህ ኩንታል ዘመናዊ ማዳበሪያ፣ 6 ነጥብ 2 ሜትር ኪዩብ ባህላዊ ማዳበሪያ እንዲሁም ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ የሰብልና የአትክልት ዘሮች ለአርሶ አደሩ ተሰራጭተዋል” ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለው የዝናብ ሁኔታ ለእርሻ ሥራው ተስማሚ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደረጄ፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ አርሶ አደሮች ማሳቸውን በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና የምርት ማሳደጊያ ግብአቶችን እንዲጠቀሙ ስልጠና መሰጠቱንም አቶ ደረጄ ገልፀዋል። እንደ ቡድን መሪው ገለጻ አርሶ አደሮቹ ከእርሻ ሥራ በተጓዳኝ በየቀበሌያቸው ተደራጅተው የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የደን ልማትና የምንጭ ማጎልበት ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ። ከአርሶ አደሮቹ መካከል የያያ ጉለሌ ወረዳየሰሌ-ግቤ ቀበሌ አርሶ አደር አመንቴ በሽር እንዳሉት ምርታቸውን ካለፉት ዓመታት በእጥፍ ለማሳደግ እየሰሩ ናቸው። ለእዚህም የተሻሻሉ የእርሻ አሰራሮችን ተግባራዊ ከማድረግ ባለፈ ለሰብላቸው ተገቢ እንከብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል። ጤፍን በመስመር መዝራታቸው፣ የተሻሻሉ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን መጠቀማቸውና የሚያደርጉት የማሳ እንክብካቤ ሥራ ምርታማነታቸውን እንደሚጨምር ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል ። አምና ጤፍን በመስመር በመዝራት በሄክታር 42 ኩንታል ምርት እንዳገኘ የገለጸው በግራር ጃርሶ ወረዳ የወርጡ ቀበሌ ሞዴል አርሶ አደር ካሳሁን ገለታ ነው። ዘንድሮ በመኸር እርሻው እጥፍ ምርት ለማግኘት ማሳውን ቀድሞ በማረስና በማለስለስ ወደስራ መግባቱን አመልክቷል። በቅርቡ በማሳው ላይ ጤፍ በመስመር ዘርቶ በመንከባከብ ላይ መሆኑንም ተናግሯል። የስርጢ ቀበሌ አርሶ አደር ማሾ በዳኔ በበኩላቸው ማሳቸው ውሃ አዘል ቢሆንም በቢ ቢ ኤም ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ ውሃውን በማጠንፈፍ ስንዴ ለማምረት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግሯል። “ከዚህ ቀደም በብተና እነዘራ የነበረውን ዘር በመስመር በመዝራት ምርታማነቴን ለማሳደግ እየሰራሁ ነው” ብሏል። ባለፈው ዓመት በሰሜን ሸዋ ዞን በመኸር ወቅት ከለማው መሬት ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ዘንድሮ ሙሉ ለሙሉ በመስመር ከተዘራው መሬት ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም