በተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ምርታማነታችንን አሳድገናል-አርሶአደሮች

144
ጎንደር ሰኔ 7/2010 የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተን በመጠቀማችን የአፈር ለምነትን ጠብቆ በማቆየት የሰብል ምርታማነታችንን ለማሳደግ አስችሎናል ሲሉ የማእከላዊ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ ለዘንድሮ የምርት ዘመን ከ120 ሺ በላይ የዞኑአርሶ አደሮች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀታቸውን የግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ሰፊ ጉልበት የሚፈልግ አድካሚ የግብርና ስራ ቢሆንም የመሬትን ለምነት ጠብቆ በማቆየት ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ የተሻለ ነው የሚሉት የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጋሻው ምትኩ ናቸው፡፡ ያለ ማዳበሪያ ስዘራ የማገኘው ቀይ ሽንኩርት ከሩብ ሄክታር 15 ኩንታል ነበር ያሉት አርሶአደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም የሚያገኙት ምርት ወደ 20 ኩንታል ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡ ''የተፈጥሮ ማዳበሪያን አንድ ጊዜ በመጠቀም ለተከታታይ ሶስት አመታት ተጨማሪ ማዳበሪያ ሳልጠቀም በቂ ምርት እያገኘሁ ነው''የሚሉት ደግሞ በምእራብ ደንቢያ የአብርጅሃ ቀበሌ ነዋሪው አርሶአደር አለኸኝ መኳንንት ናቸው፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለበቆሎ ሰብል እጅግ ተስማሚ መሆኑን የተናገሩት አርሶአደር አለኽኝ ከግማሽ ሄክታር ያገኘሁትን 35 ኩንታል የበቆሎ ምርት ለሁለት ተከታታይ አመታት  ተመሳሳይ ወጤት መሰብሰብ  ችያለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በምእራብ ደንቢያ ወረዳ የጯሂት አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር ስማቸው በላይነህ በበኩላቸው በየአመቱ በግብርና ባለሙያዎች ምክር በመታገዝ 20 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅተው እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአካባቢያችን የሚዘጋጅ በመሆኑ በወጪ ደረጃ አዋጭ ነው ያሉት አርሶአደር ስማቸው በእርሻ መሬት ላይ በቀላሉ ወደ ብስባሽነት የሚቀየር በመሆኑ አካባቢንም እንደማይጎዳ አስታውቀዋል።፡ የማእከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ አበበ አለሙ እንደተናገሩት በ2010/11 የምርት ዘመን የሚውል 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሩ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ የተፈጥሮ ማዳበሪያውን ያዘጋጁት በዞኑ 13 ወረዳዎች የሚገኙ 122ሺ አርሶአደሮች ናቸው፡፡ አርሶአደሮቹ በነፍስ ወከፍ ከ15 እስከ 20 ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ያዘጋጁ ሲሆን እስካሁንም 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትር ኩዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በእርሻ ማሳ ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል፡፡ በቆሎና ዳጉሳን ጨምሮ የጥራጥሬ ሰብሎች ለሆኑት ባቄላና አተር እንዲሁም ለድንችና ቀይ ሽንኩርት ምርታማነት መጨመር ተስማሚ የአፈር ማዳበሪያ እንደሆነም ባላሙያው ተናግረዋል፡፡ ባለሙያው እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ በዞኑ 55ሺ ሄክታር የእርሻ መሬት በተፈጥሮ ማዳበሪያ /ኮምፖስት/ የሚለማ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም