የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የቶኪዮ አሎምፒክ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ነገ ከካሜሮን አቻው ጋር ያደርጋል

91
ነሀሴ 19/2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የቶኪዮ ኦሎምፒክ የቅድመ ማጣሪያ የሁለተኛ ዙር ጨዋታውን ነገ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ከካሜሮን አቻው ጋር በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያደርጋሉ። ብሔራዊ ቡድኑ በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎን ከዩጋንዳ ጋር አድርጎ በድምር ውጤት 4 ለ 2 ማሸነፉ ይታወሳል። ውጤቱን ተከትሎ ሉሲዎቹ የሁለተኛ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ከካሜሮን ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደርጋሉ። በአሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ለጨዋታው ቅድመ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ በአዳማና በባህርዳር ከተሞች ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ ያደረገው የኦሎምፒክ ቡድኑ በአፍሪካ ካሉ ጠንካራ የሴት ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ ከሆነው የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ ፉክክር እንደሚጠብቀው ተገምቷል። ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በማቻኮስ ስታዲየም ከኬንያ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደረጉት ሉሲዎቹ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት መሸነፋቸው የሚታወስ ነው። በ47 ዓመቱ ካሜሩናዊ አሰልጣኝ አለን ጄዩምፋ የሚመራው የካሜሮን የሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ላለበት ጨዋታ ከሳምንት በፊት ባህርዳር በመግባት ልምምድ ሲያደርጉ ቆይቷል። የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ኬንያውያን ዳኞች የሚመሩት ሲሆን የጨዋታው ኮሚሽነር ከሱዳን ናቸው። የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በሶስተኛ ዙር ማጣሪያ መስከረም ወር 2012 ዓ.ም ከዴሞክራቲክ ኮንጎና ኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል። እ.አ.አ በ2020 በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ውድድር የአፍሪካ ዞን የእግር ኳስ የማጣሪያ ውድድር ከመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 25 የአፍሪካ አገሮች በማጣሪያው ውድድር ላይ እየተሳተፉ ሲሆን አፍሪካ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ሴቶች እግር ኳስ ያላት የተሳትፎ ኮታ አንድ ብቻ ነው። አምስት ዙር ባለው የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ጨዋታ በመጨረሻው ዙር የሚቀሩ ሁለት ብሔራዊ ቡድኖች በጥር ወር 2012 ዓ.ም በሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ አሸናፊው ቡድን አፍሪካን በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚወክል ይሆናል። ተሸናፊው ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፍ እና በደቡብ አሜሪካ ዞን (ኮንሜቦል) የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ ከቺሊ የኦሎምፒክ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታውን አድርጎ ወደ ቶኪዮ ኦሊምፒክ የማለፍ እድሉን የሚወስን ይሆናል። ከአዘጋጇ ጃፓን ውጪ ብራዚል፣ ኔዘርላንድ፣ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ስዊድንና ኒውዚላንድ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር መሳተፋቸውን ያረጋገጡ የሴት ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው። በቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር የሴቶች እግር ኳስ ውድድር 12 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም