ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች ያገኘችው የሜዳሊያ ብዛት አራት ደረሰ

112
ነሀሴ 19/2011 ኢትዮጵያ በሞሮኮ እየተካሄደ ባለው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች (የአፍሪካ ኦሎምፒክ) ያገኘችው የሜዳሊያ ብዛት አራት ደርሷል። በ26 የስፖርት አይነቶች ከ54ቱ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ስድስት ሺህ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት የአፍሪካ ጨዋታዎች ነሐሴ 13 ቀን 2011 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል። ትናንት በተጀመረው የብስክሌት የቡድን ሰአት ሙከራ (Team time trial) ውድድር በሴቶች ኢትዮጵያ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘቷን ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በውድድሩ ደቡብ አፍሪካ አንደኛ ደረጃ በመያዝ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን ኤርትራ ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ የብር ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች። የብስክሌት የቡድን ሰአት ሙከራ በወንዶች በቅደም ተከተል ደቡብ አፍሪካ ሩዋንዳና ኤርትራ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ሲይዙ በውደድሩ ኢትዮጵያ ስምንተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ኢትዮጵያ ትናንት በብስክሌት ያገኘችውን የነሐስ ሜዳሊያ ጨምሮ በአንድ ወርቅና በሶስት ነሐስ በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሜዳሊያ ሰንጠረዡ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ታሪኩ ግርማ በወርልድ ቴኳንዶ ከ63 ኪሎ ግራም በታች ወንዶች አሸናፊ በመሆን ለኢትዮጵያ በውድድሩ የመጀመሪያውን ወርቅ ማስገኘቱ የሚታወስ ነው። በወርልድ ቴኳንዶ ከ54 ኪሎ ግራም በታች ወንዶች ሰለሞን ቱፋ ከ53 ኪሎ ግራም በታች ሴቶች ጸባኦት ጎሳዬ ቀሪዎቹን የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኙ ስፖርተኞች ናቸው። የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ እየሆነችበት ያለ የስፖርት አይነት ነው። ትናንት ኢትዮጵያ ከምትሳተፍባቸው የስፖርት አይነቶች መካከል የቼስና የካራቴ ስፖርት ውድድሮች ተጀምረዋል። የክብደት ማንሳት ውድድር ዛሬ የሚጀምር ሲሆን የአትሌቲክስና የጅምናስቲክ ውድድሮች ነገ እንደሚጀመሩ ከውድድሩ መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል። እስካሁን ባለው ውጤት መሰረት ግብጽ በ25 ወርቅ በ33 ብር በ20 ነሐስ በድምሩ 78 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የበላይነቱን ስትይዝ፤ ደቡብ አፍሪካ በ23 ወርቅ በ15 ብር 12 ነሐስ በድምሩ 50 ሜዳሊያ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። አዘጋጇ ሞሮኮ በ13 ወርቅ 11 ብር 16 ነሐስ በድምሩ 40 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በ12ኛው አፍሪካ ጨዋታዎች ከሚሳተፉት 54 አገሮች መካከል 31 አገሮች ሜዳሊያ አግኝተዋል። በውሃ ዋና ደቡብ አፍሪካን ወክላ የምትሳተፈው ኤሪን ጋላገር ባደረገቻቸው ውድድሮች ስምንት የወርቅና ሁለት የብር በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት እስካሁን ባለው የውድድር ቆይታ ከፍተኛ የሜዳሊያ ቁጥር የሰበሰበች ስፖርተኛ ሆናለች። የአፍሪካ ጨዋታዎች ውድድር እ.አ.አ በ2020 በጃፓን ቶኪዮ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር እንደ ማጣሪያ ያገለግላል። በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ የስፖርት ልዑክ እየተሳተፈበት የሚገኘው የሞሮኮው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፎ ታሪኳ ከፍተኛ ቁጥር የሆነውን 188 ስፖርተኞች ይዛ የቀረበች ሲሆን በ13 የስፖርት አይነቶች ትሳተፋለች። አትሌቲክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ካራቴ፣ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ጅምናስቲክ፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋና፣ ባድሜንተን፣ ክብደት ማንሳት፣ ቼስና ቅርጫት ኳስ ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው። ካራቴ፣ ቅርጫት ኳስ እና ቼስ ዘንድሮ በአፍሪካ ጨዋታዎች የምትሳተፍባቸው አዲስ የስፖርት አይነቶች እንደሆኑም ይታወቃል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም