የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰባተኛው የሙት ዓመት በመቀሌ ተከበረ

353
መቀሌ ነሐሴ 19/ 2011 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰባተኛው የሙት ዓመት ትናንት በመቀሌ በፓናል ውይይት ተከበረ። የችግኝ ተከላ መርሐ ግብርም ተካሂዷል። በፓናል ውይይቱ ላይ''ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪው መዋቅራዊ ሽግግርና ኢኮኖሚያዊ ህዳሴ፣ዕድልና ተግዳሮቶች’’ በሚል ርእስ የመወያያ የመነሻ ጽሁፍ በቀድሞው የጠቅላይ ሚኒስትር የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ንዋይ ገብረአብ ቀርቧል። በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቀያሽነት የተተገበረው ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ኢትዮጵያን ከነበረበችበት ኋላቀር የኢኮኖሚ እድገትና የድህነት አረንቋ ወደ ተሻለ ልማት አሸጋግሯታል ብለዋል። በተለይ የመጨረሻዎቹ 20 ዓመታት ታላላቅ ኢኮኖሚያዊ እድገት የተመዘገበበት ነው ያሉት አቶ ንዋይ ፣በመጀመሪያው 10 ዓመት በየዓመቱ በአማካይ 4 ነጥብ 5 በመቶና በኋለኞቹ 10 ዓመታት ደግሞ ከ10 ነጥብ 5 በመቶ በላይ ዕድገት መመዝገቡን አውስተዋል። ኢኮኖሚያዊ እድገቱ በዘመን፣በቦታና በሌሎች መለኪያዎች ሲመዘን በዓለም ''እጅግ በጣም ትልቅ'' የሚባል ነው ያሉት ምሁሩ፣እድገቱም ኢትዮጵያ ከነበረችበት ደረጃ ሲታይ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የተመዘገበበት ነበር ብለዋል። እድገቱም ኮሪያና ታይዋንን የመሰሉ አገሮች በ20ና 30 ዓመታት ውስጥ ካስመዘገቡት ተመሳሳይነት እንዳለው አስረድተዋል። መዋቅራዊ የኢኮኖሚ እድገትና የአንድ አገር አጠቃላይ ልማት የረጅም ዓመታት ጥረት ውጤት ነው ያሉት አቶ ንዋይ፣ኢትዮጵያ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አመራር ሰጪነት የተመዘገበው እድገት እንደ መሸጋገሪያ መዋቅር ስኬታማ እንደነበር አመልክተዋል። ሆኖም የተመዘገበው እድገት አገሪቱ ከቆየችበት ድህነት አንጻር ሲታይ ከነብስ ወከፍ ገቢ ድርሻ ሲታይ ዝቅተኛ ነበር ብለዋል። ለኢኮኖሚ እድገቱ መሳካት እንዲያግዙ የትምህርት፣የጤና መንገድና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አቶ ንዋይ አስታውሰዋል። ግብርናውን በማልማት ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለማሸጋገር ጥረት መደረጉንና ለዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች መስፋፋታቸውን እንዲሁም የኃይል ማመንጫ ግድቦች መገንባታቸውን ተናግረዋል። በዚህም ኢትዮጵያ እንደ ሕንድ የአረንጓዴ አብዮትን ያሳካች አገር መሆኗን ተናግረዋል። ''የአገር ውስጥና የውጭ ንግድ ተቋማት መዋእለ ንዋይ ኢኮኖሚያዊ ሚናና ኢኮኖሚያዊ ህዳሴ’’ በሚል ርዕስ የመወያያ የመነሻ ጽሑፍ በጋራ ያቀረቡት ዶክተር ሙለታ ይርጋና አቶ ሚዛነክርስቶስ ዮውሃንስ በየበኩላቸው፣ኢትዮጵያ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የአመራር ጊዜ ኢንቨስትመንትንና ቁጠባን የሚያበረታቱ ሥራዎች መከናወናቸውን ይናገራሉ። በዚህም በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገሪቱ መግባታቸውንና በዚህም ለቀጣይ የኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ መሸጋገሪያ የሚሆን የኢንቨስትመንት አቅምና መደላድል መፈጠሩን አመልክተዋል። ከውስጥ ወደ ውጭ የሚመለከት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተቀርጾ ሥራ ላይ በመዋሉ ድህነትን ለማጥፋት መሰራቱንም አስረድተዋል። ሆኖም የሥራ ዕድሎች አለመስፋፋት፣የፖሊሲው አለመስረጽና ማበረታቻ ከተጠያቂነት ጋር አለመሄድና በብቁ የመንግሥት ቢሮክራሲና የፓርቲ አባላት አለመመራት ችግሮች ነበሩበት ብለዋል። የፓናል ውይይቱን ያዘጋጁት የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን፣የመቀሌ ዩኒቨርስቲና የመቀሌ ከተማ አስተዳደር ነበሩ ። የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የአረንጓዴ ልማት መርሐ ግብር ለማሰብ በሰማዕታት ሐውልት ቅጥር ግቢ በሚገኘው በስማቸው በተሰየመው ፓርክ ችግኞች ተክለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም