በክልሉ 90 ሺህ ከሚጠጉ ተሽከርካሪዎች የመድህን ዋስትና ፈቃድ ያላቸው ከ32 ሺህ አይበልጡም

66
ባህር ዳር (ኢዜአ) ነሀሴ 18 1ን 2011-- በአማራ ክልል ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ 90 ሺህ የሚጠጉ ተሽከርካሪዎች የ3ኛ ወገን የመድህን ዋስትና ፈቃድ ያላቸው ከ32 ሺህ እንደማይበልጡ ተገለጸ። በመድህን ፈንድ ኤጀንሲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዝመራው በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት በተሽከርካሪ አደጋ እየጠፋ ያለውን የሰው ሕይወትና የአካል ጉዳት ለመከላከልና ለመቀነስ ሁሉም ተሽከርካሪዎች የጸና የ3ኛ ወገን የመድህን ዋስትና ፈቃድ ሊኖራቸው ይገባል። ተሽከርካሪዎች የመድህን ዋስትና ፈቃዱ ሳይኖራቸው በመንገድ ላይ እንዳይንቀሳቀሱ የሚከለክለውን አዋጅ ጽህፈት ቤቱ ለማስፈፀምም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ከሐምሌ 10 እስከ ነሐሴ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ለአንድ ወር ባለሃብቱ፣ ድርጅቶችና የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ለተሽከርካሪዎቻቸው የ3ኛ ወገን መድህን ዋስትና ፈቃድ ሳያወጡ እንዳያሽከረክሩ በንቅናቄ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሲሰራ ቢቆይም አፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል። ችግሩን ለመፍታት የተሽከርካሪ ባለንብረቶችና ሁሉም ተቋማት በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው የ3ኛ ወገን የመድህን ዋስትና ፈቃድ እንዲያወጡ በክልል ደረጃ በቅርቡ አቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደስራ መገባቱን ገልጸዋል። አቢይ ኮሚቴው ጽህፈት ቤቱን ጨምሮ ከፖሊስ፣ ከመንገድና ትራንስፖርት፣ ከኢንሹራንሶችና ከሌሎች የተውጣጡ አካለት የተካተቱበት መሆኑን ጠቁመዋል። እንደ አቶ አዝመራው ገለጻ ኮሚቴው እስካሁን የመድህን ዋስትና ፈቃድ ያላወጡ ባለንብረቶች ለተሽከርካሪዎቻቸው ፈቃድ አውጥተው ወደ ስራ እንዲገቡ ቅስቀሳና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ያከናውናል። በ2011 በጀት ዓመት በተሽከርካሪ የትራፊክ አደጋ ለደረሰባቸው 6 ሺህ ለሚጠጉ ተጎጂዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጭ አድርጎ ማሳከሙን አስታውሰዋል። ከተጎጂዎች መካከል ኢንሹራንስ በሌላቸውና ገጭቶ ባመለጡ ተሽከርካሪዎች የተገጩት 16 ሰዎች ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ አምስቱ አስፈላጊውን ማስረጃ በማሟላታቸው በጠቃላይ ከ235 ሺህ ብር በላይ የካሳ ክፍያ መፈፀሙን ገልጸዋል። እንደ አቶ አዝመራው ገለጻ አንድ ተሽከርካሪ የፀና የ3ኛ ወገን የመድህን ዋስትና ፈቃድ ሳይኖረው በመንገድ ላይ ማሽከርከር በብር ከ3ሺህ እስከ 5ሺህ፣ በእስራት ደግሞ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት እንደሚያስቀጣ በአዋጅ ተቀምጧል። የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ውቤ አጥናፉ በበኩላቸው በክልሉ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከልና የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አንደሚገባ አስገንዝበዋል። የንቅናቄ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በክልል ደረጃ የተቋቋመው አቢይ ኮሚቴ ባለሃብቱ በቂ ግንዛቤ ኖሮት የ3ኛ ወገን መድህን ዋስትና ሳያወጣ እንዳያሽከረክር የተጠናከረ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል። “ከዚህ ቀደም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራው በሚፈለገው ልክ አለመሰራቱ በክልሉ የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ እንዲባባስ አድርጓል” ያሉት ደግሞ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ ንዑስ የሥራ ሂደት መሪ ኮማንደር አምሳሉ ገብረ መድህን ናቸው። ኮማንደር አምሳሉ እንዳሉት አንዳንድ አሽከርካሪዎች ጉዳት አድርሰው ሲሰወሩ ሰብአዊነት ተሰምቷቸው ተጎጂዎችን ወደ ህክምና ተቋማት ወስደው በራሳቸው ወጪ የሚያሳክሙም አሉ። ይህም አሽከርካሪዎችም ሆኑ ህብረተሰቡ ስለ 3ኛ ወገን መድህን ዋስትና በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸው የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው “በቀጣይ ችግሩን ስርነቀል በሆነ መንገድ ለመፍታት የግንዛቤ ስራውን ማጠናከር ይገባል” ብለዋል። በቀጣይም ሁሉም የአሽከርካሪ ባለንብረቶችና ተቋማት የጸና የ3ኛ ወገን መድህን ዋስትና በማውጣት የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቀነስ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። በክልሉ በ2011 በጀት ዓመት በደረሰ የትራፊክ አደጋ በ1 ሺህ 109 ሰዎች ሞትና በ2ሺህ 367 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላይ የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን ግምቱ 97 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረት መውደሙ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም