የገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከላት ''ተገቢውን ስልጠናና ድጋፍ ''አያደርጉልንም ''-የትግራይ አርሶ አደሮች

101
መቐለ ነሐሴ 16 ቀን 2011 በትግራይ የሚገኙ የገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከላት ''ተገቢውን ስልጠናና ድጋፍ ''እንደማያደርጉላቸው አንዳንድ አርሶ አደሮች ገለጹ። የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ በበኩሉ፣ማዕከላቱ የአመራሩ ድጋፍ ስለማያገኙ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ክፍተት አለባቸው። ከአሥር ዓመታት በፊት የተቋቋሙት ማዕከላት የክህሎት ክፍተታቸውን ስለማይሞሉላቸው ግብርናውን ለማዘመን እንዳልቻሉ አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል። በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ የባርካ ገጠር ቀበሌ አርሶአደር ኃይለ ሥላሴ  ተስፋይ  እንዳሉት በአቅራቢያቸው ድጋፍ እንዲያደርግላቸው የተከፈተው  ማዕከል  የሚሰጣቸው ስልጠና የጠበቁትን ያህል አይደለም። ማዕከሉ ለባለሙያዎች በማዳበሪያ አጠቃቀም፣ በመሥመር መዝራትና  እርጥበት የማከማቸት ፋይዳ በዛፍ ጥላ ሥር ትምህርት እንደሚሰጧቸው ተናግረዋል። ከዚህ ያለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ሌሎች ግብርናን የሚያዘምኑ ስልጠናዎች በባለሙያዎቹ እንደማይሰጣቸውና ማዕከላቱ ሲገነቡ ይሰጣሉ የተባሉትን ዓላማ  እንዳላሳኩ አርሶ አደር ኃይለሥላሴ ገልጸዋል። ‘’በቀበሌያቸው ውስጥ የሚገኘው የገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከል የተግባር ልምምድ የሚካሄድበት ማሳ በአቅራቢያው የለውም ያሉት ደግሞ በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን በእንደርታ ወረዳ የፈለገሰላም ቀበሌው  አርሶ አደር አሰፋ ግርማይ ናቸው። ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሄደው መልካም ተሞክሮዎችና ልምድ ለመቅሰም አማራጮች እንዳልተዘጋጁላቸው ገልጸዋል። በበጋ ወቅት አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር የወረዳ አመራሮች ከአርሶአደሩ ጎን ሆነው በቅርበት የሚደግፉበት ሁኔታ አይታይም ነው ያሉት አርሶ አደር አሰፋ። በየደረጃው ያሉት አመራሮች ማዕከላቱ በተገነቡበት ወቅት የነበራቸው ተነሳሽነት እየተዳከመ መምጣቱን ገልጸዋል። በአቅራቢያቸው የተቋቋመው  ማዕከል የተሟላ  ግብዓቶች እንደሌሉት ተናግረዋል። በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በዓድዋ ገጠር ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ፀጋይ ክንፈ በአካባቢያቸው  የሚገኘው  ማዕከል በመሥመር መዝራትና በማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎች እንዳልተሰጧቸው ተናግረዋል። ስልጠናው አርሶ አደሩ የሚከተለውን የግብርና አሰራራቸውን እንደማይቀይር ገልጸዋል። በመሆኑም ማዕከላቱ አሰራራቸውን ለማሻሻል ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ድጋፍና ክትትል  ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል። በትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አበራ ከደነው የክልሉ የገበሬዎች ማሰልጠኛ ማዕከል የግብርና አሰራር  የሚያግዝ  ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል። በክልሉ 677 ማዕከላት ቢኖሩም  አርሶ አደሩን  በተግባር  የተደገፈ ስልጠና በሚሰጥ ቁመና እንዲጠናከሩ  አለመደረጉ  ዋነኛ  ክፍተታቸው ነው  ብለዋል ዳይሬክተሩ። ከማዕከላቱ መካከል የማስተማሪያ ክፍሎች ያላቸው ከ10እንደማይበልጡና አብዛኛዎቹ ሥልጠናው በዛፍ ጥላ ሥር እንደሚሰጡ አመልክተዋል። ከዚህ አልፎም 504 የሚሆኑት ማዕከላት ለአርሶ አደሩ የተግባር ስልጠና ለመስጠት የሰርቶ ማሳያ ቦታ እንደሌላቸው አቶ አበራ ተናግረዋል። ከማዕከላቱ 402 የሚሆኑትም ሰርቶ ማሳያዎች  የሚቀመጡበትና በአርሶ አደሮቹ ለመጎብኘት ምቹነት የላቸውም ብለዋል። በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ማዕከላት ግን አርሶ አደሩ የአቅም ክፍተት  ለመሙላት  እየሰሩ  መሆናቸውን  ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ በተለይ  በጠብታ መስኖ፣ በመሥመር  መዝራትና  በተፈጥሮ  ሃብት ጥበቃ ሥራዎች የተሻለ  ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል። ማዕከላቱ ከተቋቋሙለት ዓላማ ጋር ሲነፃፀር ክፍተት የሚታይባቸው በየደረጃው ያለው አመራር ድጋፍ በማነሱ መሆኑን  አቶ አበራ አስረድተዋል። በክልሉ ካሉት 200 ማዕከላት ክትትልና ድጋፍ ለማድረግና ቁሳቁስ ለማሟላት መታቀዱን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም