''የአሸንዳ በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብና የኩራት፣ የማንነትና የገቢ ምንጭ እንዲሆን መሥራት ይገባል''-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

96
ነሐሴ 16/2011 የአሸንዳ በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብና የኩራት፣ የማንነትና የገቢ ምንጭ እንዲሆን መሥራት እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ። ዓመታዊው የልጃገረጆች ጨዋታ የአሸንዳ በዓል ዛሬ በመቀሌ ባሎኒ ስታዲዬም እየተከበረ ነው። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በበዓሉ ላይ እንደተናገሩት በዓሉን ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝና የኢትዮጵያውያን  ማንነት መገለጫና የገቢ ምንጭ እንዲሆን ጥረት ሊደረግ ይገባል። በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረው ውብ ባህል በቀጣይ እንደ መስቀል፣ ፊቼ ጨምበላላና ገዳ ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ)ተመዝግቦ ዓለም አቀፍ ቅርስ ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። የትግራይ ክልል ሕዝብ ይህንን ዕውንን ለማድረግ እየተጫወተው ላለው ግንባር ቀደም ሚና አመስግነዋል። አገሪቱ  በተመዘገቡ ቅርሶች ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃ መያዟን ያወሱት ፕሬዚዳንቷ፣ ነገር ግን ምዝገባ ግብ ስለማይሆን እንክብካቤና ጥበቃ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ባህልን ጠብቀንና ተንከባክበን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ከቻልን ዛሬ ከሆኑት በላይ የኩራት፣ የማንነትና የገቢ ምንጮች እንደሚሆኑ አያጠራጥርም  ብለዋል። ኢትዮጵያ የበርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ታረካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፣ ባህልና ቅርሶች የአገሪቱን ሕዝቦች እርስ በእርሳቸው ከሌላው ዓለም ማህበረሰብ ጋር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር ጠቀሜታ እንዳላቸው አመልክተዋል። የአሸንዳ በዓል አንዱ የእኩልነት ማሳያ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ሴቶች በዚህ በዓል የተሰጣቸውን ነፃነት በዓመቱ 365 ቀናት ሊያገኙ ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል። የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው የአሸንዳ በዓል የማይዳሰስ  ቅርስ ሆኖ ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ለዚህም የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። ትግራይ የበርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህል ባለቤት ስትሆን ከነዚህ ውስጥ አንዱ አሸንዳ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ደብረጽዮን፣በዓሉ  ሳይበረዝና ሳይከለስ  ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም