የኢትዮጵያ የሽግግር ጊዜ ስኬታማ እንዲሆን ቃልን ወደ ተግባር መቀየር ያስፈልጋል - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

60
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 16/2011 የኢትዮጵያ የሽግግር ጊዜ ስኬታማ እንዲሆን ንግግሮችን ከቃል ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ላይ በአዲስ አበባ እየመከረ በሚገኘው መድረክ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ቃልን ወደተግባር መቀየር ተገቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል። በንግግራቸው ''ኢትዮጵያ የያዘችውን መሰረታዊ ለውጥ ለማሳካት ሰላምና መረጋጋት መከበር፣ የህግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት'' ሲሉ ገልጸዋል። በችግሮች ዙሪያ የሚደረገው ንግግር ግልጽና እውነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንደሚገባውም አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ከሚስተዋሉ ችግሮች አንዱ ንግግሮችን ወደ መሬት የማውረድ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ያለውን የሽግግር ጊዜ እውን ለማድረግ ከንግግር ያለፈ ተግባር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ሌሎች አገሮች በለውጥ ሂደት ያሳለፏቸውን ተመሳሳይ ሁኔታዎች መማር ጠቃሚ ቢሆንም ከነባራዊ ሁኔታው ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ አገር በቀል ሃሳቦች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። በምሁራን መካከል የሚደረግ ውይይት የመፍትሄው አካል እንዲሆን ለማስቻል የውይይት ሃሳቡን ወደ ህብረተሰቡ ማውረድ እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንቷ በአጽንኦት አንስተዋል። 'በአገራችን ሰላም ያገባናል' በማለት በተነሳሽነት የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እርስ በርሳቸው መናበብና መቀናጀት እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መረጋጋት አስፈላጊነት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአካባቢዋና አህጉራዊ መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ "በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን ብዝሃነት ማስተናገድ የምንችልበትና የምንስማማበት የአሰራር ስርአት ያስፈልገናል" ብለዋል። የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ ባደረጉት ንግግር ''ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ቀደም ሲል፣ አሁንና ወደ ፊት ወሳኝ ጠቀሜታ አላት'' ብለዋል። በታሪክ ለአፍሪካ የነጻነት ምሳሌ ተደርጋ የምትታየው ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ያጋጠማትን ተግዳሮት አሸንፋ መውጣት እንዳለባት ተናግረው፤ በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ለአህጉሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ወሳኝ መሆኑን አስቀምጠዋል። በኢትዮጵያ የለውጥ ታሪክ የተከናወኑ ዋና ዋና ክንውኖችን በዳሰሰው ንግግራቸው ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን የነጻነት ምሳሌ መሆኗን አንጸባርቀዋል። በደቡብ አፍሪካ በነበው የለውጥ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ እርምጃዎችን የሚያሳይ ሃሳብ በንግግራቸው አንስተዋል። በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ባሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ላይ እየመከረ በሚገኘው መድረክ ላይ አለም አቀፍ ተሞክሮዎች፣ ቀደም ሲል በነበሩ ለውጦች የተገኙ ስኬቶችና ችግሮች ሰፊ ሃሳብ ተነስቷል። የመጣው ለውጥ ያለበት ሁኔታና አስፈላጊነት እንዲሁም የወደፊት አቅጣጫዎችና ተግዳሮቶች  ላይ ያተኮሩ ጽሁፎች ከተለያዩ አገሮች በመጡና በኢትዮጵያውያን ምሁራን ይቀርባል። ዛሬና ነገ በሚካሄደው በዚህ የምክክር መድረክ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የሲቪል ማህበራትና ሌሎች የሚመለከታቸው 200 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም