በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በከፍተኛ እርጥበት ሳቢያ የጸረ - ሰብል ተባይ ሊከሰት እንደሚችል ተጠቆመ

62
ነሐሴ 16/2011 በቀጣዮቹ 10 ቀናት በሚኖር ከፍተኛ እርጥበት ሳቢያ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የጸረ - ሰብል ተባይ ሊከሰት ስለሚችል አርሶ አደሩ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ አሳሰበ። ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግላጫ እንዳሳሰበው፤ በቀጣዮ አስር ቀናት የመኸር አምራች በሆኑ አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ እርጥበት ያለው ዝናብ እንደሚኖር ተተንብይዋል። እርጥበቱ በተለያዩ የዕድገት ደረጃ ላሉ ሰብሎች ጠቃሚ ቢሆንም በማሳ ላይ ውሃ በበዛባቸው አካባቢዎች ለአረምና ለጸረ- ሰብል ተባይ የመጋለጥ ዕድል እንደሚኖር አመልክቷል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ችግሩን ለመከላከል ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል። በውሃ ብዛት በሚጠቁ አካባቢዎች አርሶ አደሩና የግብርና ባለሙያዎች ውሃው በማሳ ላይ እንዳይተኛ የውሃ ማስኬጃ ቱቦዎችን በመስራት ችግሩን አስቀድሞ እንዲከላከሉ አሳስቧል። በተጨማሪም አረምን በወቅቱ በማረምና ጸረ-አረምና የፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን በወቅቱ በመጠቀም መከላከል እንደሚገባ ትንበያው አመልክቷል። ኦሞ ጊቤ፣ ተከዜ፣ አባይ፣ ባሮአኮቦ፣ የታችኛውና የመካከለኛው አዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ አባይና አዋሽ አዋሳኝ ከፍተኛ ቦታዎች የላይኛው ሸበሌ፣ ገናሌና ዳዋ ተፋሰሶች ከፍተኛ እርጥበት የሚጠበቅባቸው መሆናቸውን ኤጀንሲው ገልጿል። በአንዳድ አካባቢዎች ከቅጽበታዊ ጎርፍና የወንዞች ሙላት እንዲሁም በተፋሰሶች አካባቢ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባው አሳስቧል። በአጠቃላይ በቀጣዩ አስር ቀናት የክረምት ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች በመጠንና በስርጭት የተሻለ  እርጥበት ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም