በኢትዮጵያ የሊድ-አሲድ ባትሪ አያያዝና አሰባሰብ ስርዓት ካልተበጀለት አደጋ ያስከትላል ተባለ

81
ነሐሴ16/2011  በተሽከርካሪ ባትሪ ውስጥ የሚገኘውና ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ሊወገድ የሚገባው የሊድ-አሲድ አያያዝና አሰባሰብ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ካልተመራ በሰው ጤናና የአካባቢ ደህንነት ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የኢትዮጵያ አካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አሳሰበ። በኢትዮጵያ ከአደገኛ ቆሻሻዎች መካከል የሚመደበው ባለ-ሊድ አሲዳማ ባትሪ በሁሉም ተሽከርካሪዎችና በፀሃይ ሃይል በሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል። ሆኖም ጥቅም ላይ የዋለውን የሊድ-አሲድ ባትሪ በማሰባሰብ እንደገና መጠቀም የሚቻልበትን መንገድ ለመዘየድ ወይም ለማስወገድ የሚደረገው እንቅስቃሴ ደካማ መሆኑን ነው የኢትዮጵያ አካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የገለፀው። በኮሚሽኑ ፖሊሲ ህግና ደረጃዎች ጥናትና ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ አየለ ኤገና እንደተናገሩት የሊድ አሲድ በአግባቡ ካልተያዘ ለሰው ጤና፣ ለአካባቢ ብክለት፣ ለብዝሃ ህይወት መዛባትና ለኢኮኖሚ ልማት እንቅፋት ይሆናል። አቶ አየለ ይህንን የተናገሩት በችግሩ ላይ የመከረውና ኮሚሽን ከጀርመን የልማት ድርጅት ኢነርጃይዚንግ ዴቨሎፕመንት (GIZ) ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ውይይት ላይ ነው። ችግሩ በተለይ የሊድ አሲዱን  በሚያሰባስቡ፣ በሚያከማቹና ሌሎች ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ አካላት ላይ የከፋ ሊሆን ይችላል ሲሉም ነው አቶ አየለ ያመለከቱት። ላለፉት በርካታ ዓመታት የፖሊሲ ማእቀፍን ጨምሮ ችግሩን ለመቋቋም  የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅትም ከችግሩ ጋር በተያያዘ የአካባቢ ደህንነት ስጋትን ለመቀነስ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል ብለዋል። 'ፓን ኢትዮጵያ' የተሰኘውና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራው ግብረ ሰናይ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታደሰ አመራ በበኩላቸው ባለሊድ አሲድ የአገልግሎት ዘመኑ ካበቃ በኋላ መልሶ በማሰባሰብና በማከማቸት ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ይቻላል ብለዋል። በመሆኑም ሊድ-አሲድ ባትሪን በአግባቡ በመሰብሰብና በወጉ በመያዝ ዳግም ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። ይህም አሲዱ የሚያስከትለውን ጉዳት ከመከላከል ባሻገር ለአገር ኢኮኖሚ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲጫወት ማድረግ ይቻላልም ሲሉ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም