ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት መሪ ለሆኑት ሌተናል ጀነራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሀን መልዕክት አስተላለፉ

113
ነሐሴ 16/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት መሪ ሆነው ለተመረጡት ሌተናል ጀነራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሀን የእንኳን ደስ አለዎት መልእክት አስተላለፉ። ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሀን የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት መሪ ሆነው ትናንት የተመረጡ ሲሆን ምክር ቤቱም ከነጻነትና ለውጥ ሃይሎችና ወታደሮች 11 አባላትን ያቀፈ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሌተናል ጀነራሉ በመመረጣቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም የሽግግር መንግስት ስምምነት ፊርማን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለተመረጡት አብደላ ሀምዶክም የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ሌሎች የአፍሪካ አገራት መሪዎች በተገኙበት ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በካርቱም የሱዳን ወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤትና የነጻነት የለውጥ ሃይሎች የሽግግር መንግስት ፊርማ መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። ሌተናል ጀነራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሀን የሚመሩት ምክር ቤት በሽግግር መንግስት ስምምነት ፊርማው መሰረት ለቀጣይ ሶስት ዓመታት ሱዳንን የሚመራ ይሆናል። በመሆኑም በአገሪቷ ምርጫ እስከሚካሄድ ወታደሮቹና የነጻነትና ለውጥ ሃይሎች እየተፈራረቁ ይመራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አብደላ ሀምዶክ  20 አባላት ያሉት ካቢኔያቸውን ለማሳወቅ የ20 ቀናት ጊዜ አላቸው። በተደረሰው ስምምነት መሰረት የአገር ወስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እና መከላከያ ሚኒስትር የሚሆኑትን የሚመረጡት ግን በሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ነው። ከአራት ወራት በፊት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አል በሽር ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ በአገሪቷ የነበረው አለመረጋጋትና ህዝባዊ ተቃውሞ መፍትሄ እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች። ኢትዮጵያ በሱዳን ያለው ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ አምባሳደር መሐመድ ድሪርን የወከለች ሲሆን አምባሳደሩም ከአፍሪካ ህብረት ተወካዮች ጋር ሆነው ሁለቱ አካላት ከስምምነት እንዲደርሱ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም