በክልሉ ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያስችል ማበረታቻ እየተደረገ ነው- ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ

61
ነሐሴ 16/2011 በኦሮሚያ ክልል ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያበረታቱ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና የብሪታኒያ የዓለም ዓቀፍ ልማት ሚኒስትር አሎክ ሻርማ በኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ጉብኝት አድርጓል። በጉብኝቱ ወቅት አቶ ሽመልስ እንዳሉት በክልሉ በርካታ ባለሃብቶችን ለመሳብና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እየተሰራ ነው። የውጭ ባለሃብቶችም በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያስችል ማበረታቻ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል። በመሆኑም ክልሉን የበርካታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ይበልጥ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። እንደ አቶ ሽመልስ ገለፃ የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካ አገራት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ቢያደርጉ አትራፊዎች ይሆናሉ። የብሪታኒያ የዓለም ዓቀፍ ልማት ሚኒስትር አሎክ ሻርማ የብሪታኒያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እናደርጋለን ብለዋል። በአገሪቷ የተመለከቱትን ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴም መልካም ጅምር በማለት አድንቀዋል። ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የበለጠ ተቀራርቦ ለመስራት ፍለጎት መኖሩን የገለጹት ሻርማ በቀጣይ በየደረጃው ካሉ ሃላፊዎች ጋር እንመክራለን ብለዋል። በኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ተቀጥረው ከሚሰሩት ሴቶች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው እንዳሉት በተፈጠረላቸው የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል። በተፈጠረላቸው የስራ እድል ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን እየደጎሙ መሆኑንም ተናግረዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ እና አሎክ ሻርማ ከጉብኝታቸው በኋላ በዱካም ከተማ ችግኝ ተክለዋል። በከተማዋ ነዋሪዎችም የኦሮሞ ባህልን የሚገልጹ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም