የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ለአዲሱ ትምህርት ዘመን ዝግጅታቸውን እያገባደዱ ነው

54
ነሀሴ16/2011መጪውን የትምህርት ዘመን ሠላማዊና አገልግሎት አሰጣጣቸውንም የተሻለ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኃላፊዎችና የቦርድ አመራሮች ተናገሩ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶችና የስራ አመራር ቦርድ ኃላፊዎች እንደገለጹት የትምህርት ተተቋማቱን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የሚፈቱ የዝግጅት ስራዎችን እየከወኑ ነው። የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ምስራቅ መኮንን በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎች አገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል፣ የመምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችን አቅም የመገንባትና ሌሎች ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ዶክተር ምስራቅ ገለጻ የቦርድ አመራር አባላቱ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የዩኒቨርሲቲውን ሠላም ለማስጠበቅ ይሰራሉ። ቦርዱ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል። የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንትና የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል ዶክተር ኤላዛር ታደሰ በበኩላቸው የተቋማቱን ውስጣዊ ችግሮች በመፍታትና ተጠያቂነትን በማስፈን 'መጪውን የትምህርት ዘመን የተሻለ ለማድረግ እንሰራለን' ብለዋል። ሠላማዊ የመማር ማስተማር ተግባር አጠናክረው ለማስቀጠል እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀንዓ ናቸው። በአገሪቱ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ደረጃ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ማሻሻያ፣ የተጠያቂነት አሰራርና ሌሎች የሪፎርም ስራዎች እንደሚተገበሩ ተነግሯል። ከሪፎርም ስራዎቹ መካከል አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ በትምህርት ዘመኑ ተግባራዊ እንደሚደረግ ታውቋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም