ኢንዶኔዥያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች

57
ነሐሴ 16/2011 ኢንዶኔዥያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር አል ቡሽራ ባሰኑር ገለፁ። አምባሳደሩ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በአውሮፓዊያን የዘመን ቀመር በ1961 የተመሰረተው የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በምጣኔ ኃብት፣ በማህበራዊ ልማትና ባህል ዘርፎች በከፍተኛ ፍጥነት እድገት አሳይቷል። ''በአሁኑ ወቅት አምስት የኢንዶኔዥያ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለንዋያቸውን አፍስሰው በተለያየ የልማት ዘርፍ ተሰማርተው ይገኛሉ'' ያሉት አምባሳደሩ ሌሎች በርካታ የአገሪቱ ባለኃብቶች ወደኢትዮጵያ በመምጣት ሥራ የመጀመር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል። የኢንዶኔዥያ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፉ አዲስ አበባ የሚገኘው ኤምባሲ ጠንክሮ እየሰራመሆኑን አስረድተዋል። በዚህም የሁለትዮሽ የምጣኔ ኃብት ግንኙነትቱን ከፍ ማድረግ የሚቻል መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል። ''የአገሮቹን ትብብርና መቀራረብ ማጎልበት እንዲቻል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው'' የሚሉት አምባሳደር አል ቡሽራ ባሰኑር በመጪው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በኢንዶኔዥያ የንግድ ኤክስፖ ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰዋል። በዚህ ኤክስፖ ላይ ለመሳተፍ እስካሁን 20 ኩባንያዎች መመዝገባቸውንም ጠቁመዋል። ''በአዲስ አበባም ተመሳሳይ ኩነት ይዘጋጃል'' ብለዋል። በአገሮቹ ህዝቦች መካከል የቆየውን የባህልና ማህበራዊ ግንኙነት ማጠናከር እንዲቻልም የወጣቶች የጉብኝት መርሃ ግብሮች እንደሚዘጋጁ አምባሳደሩ አመልክተዋል። በመጪው ዓመት 20 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወደኢንዶኔዥያ የሚላኩ መሆኑንም አንስተዋል። ''በተመሳሳይ የኢንዶኔዥያ ወጣቶችም ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ይደረጋል'' ብለዋል። አምባሳደሩ እንዳሉት፤ በሁለቱ አገሮች ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የትብብር ግንኙነት መፍጠር ሌላው ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ነው። በዚህም መሰረት ኤምባሲው ከሀዋሳ፣ ደሴና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተባብሮ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ ነው። ከኤምባሲው በተገኘው መረጃ መሰረት እ.አ.አ በ2017 የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ መጠን 293 ነጥብ 37 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ኢትዮጵያ በዋናነት የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስና የንፅህና መጠበቂ ቁሳቁሶችን ከኢንዶኔዥያ ስታስገባ የግብርና ምርቶችን ደግሞ ትልካለች።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም