ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች የመጀመሪያውን ሜዳሊያ አገኘች

107
ነሀሴ16/2011 ኢትዮጵያ በሞሮኮ እየተካሄደ በሚገኘው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች። በ26 የስፖርት አይነቶች ከ54ቱ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ስድስት ሺህ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት የአፍሪካ ጨዋታዎች ከትናንት በስቲያ መጀመሩ ይታወሳል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፎ ታሪኳ ከፍተኛ ቁጥር የሆነውን 188 ስፖርተኞች በሞሮኮው ውድድር ላይ አሳትፋለች። የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በ13 የስፖርት አይነቶች ይሳተፋል። ወርልድ ቴኳንዶ፣ አትሌቲክስ፣ ካራቴ፣ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ጅምናስቲክ፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋና፣ ባድሜንተን፣ ክብደት ማንሳት፣ ቼስና ቅርጫት ኳስ ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው። ትናንት በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ከ53 ኪሎ ግራም በታች ሴቶች ጸባኦት ጸጋዬ የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን ለኢትዮጵያም በአፍሪካ ጨዋታዎች የመጀመሪያው ሜዳሊያ መሆኑን ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ጸባኦት ጸጋዬ በመጀመሪያ ዙር ጨዋታዋ የዴሞክራቲክ ኮንጎዋን ሙአካ ማሴሌ ግሎዲን፣ በሩብ ፍጻሜ ቱንዚያዊቷን ቤን አሊ ራህማን ማሸነፍ ችላለች። በግማሽ ፍጻሜው ከናይጄሪያዊቷ ተወዳዳሪ ንዎሱ ቺናዙም ሩት ጋር ባደረገችው ጨዋታ ተሸንፋ በአጠቃላይ ድምር ውጤት ጸባኦት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች። ናይጄሪያዊቷ ንዎሱ ቺናዙም ሩት ከ53 ኪሎ ግራም በታች የፍጻሜ ጨዋታ ሞሮኳዊቷን ኤል ቡችቲ ኡማይማን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን ኤል ቡችቲ ኡማይማ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች። ኢትዮጵያ ከምትሳተፍባቸው 13 የስፖርት አይነቶች በአምስቱ በወርልድ ቴኳንዶ፣ በቦክስ፣ ውሃ ዋና፣ ጠረጴዛ ቴኒስና 3 በ 3 የሴቶች ቅርጫት ኳስ ውድድሮች  ትናንት ተጀምረዋል። 3 በ 3 ቅርጫት ኳስ ጨዋታው የሚካሄደው በአንድ ቅርጫት ከመደበኛው የቅርጫት ኳስ ሜዳ በግማሽ ባነሰ ሜዳ ላይ ሲሆን በእያንዳንንዱ ቡድን ሶስት ሶስት ተጫዋቾች በአንዷ ቅርጫት ላይ ነጥብ የሚያስቆጥሩበት የውድድር አይነት ነው። በውድድሩ እስካሁን ባለው ውጤት ግብጽ በ8 ወርቅ በ12 ብር በ10 ነሐስ በድምሩ 30 ሜዳሊያዎች በመሰብሰብ የሜዳሊያ ሰንጠረዡን ስትመራ አልጄሪያ በ7 ወርቅ በ6 ብር በ8 ነሐስ በድምሩ በ21 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ደቡብ አፍሪካ በ7 ወርቅ በ5 ብር በ2 ነሐስ በድምሩ 14 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን አዘጋጇ ሞሮኮ በ5 ወርቅ በ9 ብር በ7 ነሐስ በድምሩ በ21 ሜዳሊያዎች አራተኛ ደረጃን ይዛለች። በአፍሪካ ጨዋታዎች ከሚሳተፉት 54 አገራት 28ቱ ሜዳሊያ ያገኙ ሲሆን ኢትዮጵያ በአንድ ነሐስ 20ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ካራቴ፣ ቅርጫት ኳስ እና ቼስ ዘንድሮ በአፍሪካ ጨዋታዎች የምትሳተፍባቸው አዲስ የስፖርት አይነቶች ናቸው። የአፍሪካ ጨዋታዎች /የአፍሪካ ኦሎምፒክ/ የሚባለው ውድድር እ.አ.አ በ2020 በቶኪዮ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር ለመሳተፍ እንደ ማጣሪያ ውድድር የሚያገለግል ነው። በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ የስፖርት ልዑክ እየተሳተፈበት የሚገኘው የሞሮኮው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይዘልቃል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም